ቀጥታ፡

በወላይታ ዞን ሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለመሸፈን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ወላይታ ሶዶ ፤ ነሐሴ 5/2018(ኢዜአ)፦በወላይታ ዞን ለሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የወላይታ ዞን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ሶርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በወላይታ ዞን ለሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ  አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በተለይም ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ሀብት የማሰባሰብና ሰብል የማምረት ሥራው ተጠናክሮ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለዚህም ከ14 ሺህ 600 ኩንታል በላይ የእህል ክምችት መኖሩን ጠቁመው ምግብ ነክ ያልሆኑ ግብዓቶችም የድጋፍ ማሰባሰብ ተግባሩ አካል ሆነው እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ የመያዝ አቅም ባላቸው ሁለት መጋዘኖች እህል የማከማቸት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው እስካሁን 184 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

የሀብት ማሰባሰቡም ሁሉንም አካላት በማሳተፍ እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊው እስከ ታህሣሥ 2019 ዓ.ም ባሉት ወራት 134 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በ2 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ ላይ 200 ሺህ ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ በዘር የመሸፈን ሥራው በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በዞኑ ባሉ 26 መዋቅሮችም ከ5 ሺህ ኩንታል በላይ የሚይዝ መጋዘን ተገንብቶ በተደራጀ መልኩ እህል የማሰባሰብና ሀብት የማከማቸት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የዞኑ ዳሞት ሶሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉቀን መሸሻ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በወረዳው ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው።

ከወረዳው የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ የኅብረተሰቡን የመረዳዳት የቆየ ባህል ለማጎልበት በተከናወነ ተግባር፣ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን ተናግረዋል።


 

በወረዳው በተዘጋጀ መጋዘን እስካሁን ድረስ ከ1 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡንና 30 ሄክታር መሬት በበቆሎ እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በወረዳው የሚከሰቱ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቋቋም፣ የአደጋ ሥጋትን መነሻ ያደረጉ የመከላከል ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ደግሞ የዱጉና ፋንጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘካሪያስ ዎንታሞ ናቸው።

ነዋሪውን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ የሃይማኖት ተቋማትንና የሲቪክ ማኅበራትን በማሳተፍ ሀብትና እህል የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

እስከ አሁን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይና ከ308 ኩንታል በላይ እህል መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ለዚሁ ዓላማ በመኸር ወቅት ለማምረት ከታቀደው 130 ሄክታር ማሳ ውስጥ 93 ሄክታሩ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑንም አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም