ዓባይና ቀይባህር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የሚያረጋግጡ መሠረቶች ናቸው - ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዓባይና ቀይባህር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የሚያረጋግጡ መሠረቶች ናቸው - ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ) ፦ ዓባይና ቀይባህር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የሚያረጋግጡ መሠረቶች ናቸው ሲሉ የውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዓባይና ቀይ ባሕር በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የማይነጣጠሉና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።
ሁለቱ ውሀዎች በቀጣናው የፖለቲካ ካርታ ላይ የኃይል ሚዛን የሚወሰንባቸው ስትራቴጂካዊ የውሀ አካላት ናቸው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ለማረጋገጥ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በተከተለ መልኩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች ።
የውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ዓባይና ቀይባህር የኢትዮጵያን እጣፈንታ ሲወስኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያን ሕልውና ከእነዚህ የውሀ አካላት ጋር ከፍተኛ ቁርኝነት እንዳለውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳታለማና እንዳትጠቀም የውጭ ሃይሎች በተለያዩ መንገዶች ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተው፤ በተመሳሳይ በሴራ ከቀይ ባህር እንድትርቅ በማድረግ ኢትዮጵያውያን ብዙ ዋጋ ሲከፍሉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
በህዳሴ ግድብ አማካኝነት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት ከነበረው ህልማቸው መካከል አንዱን ማሳካት መቻሉን ገልጸው፤ ይህም በኢትዮጵያውያን ላይ ይደርስ የነበረውን ተጽዕኖ መስበር ያስቻለ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገሪቷ ላይ ሲደረጉ የቆዩ ደባዎችን ማስቀረት የቻለ የኢትዮጵያውያን ኩራት መገለጫ ፕሮጀክት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባህርን በተለያየ ሴራ እና ተንኮል እንድታጣ ከተደረገ በኋላ ይህንን ጉዳይ ማንሳት የማይፈቀድ እና ሌላ ስም የሚያሰጥ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የባህር በር ባለቤትነቷን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማግኘት አለብኝ ብላ ያነሳችው ጥያቄ ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይ የመንግስት ወይም የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ጉዳይ ሳይሆን ትውልድ ተሻጋሪ ስራ መሆኑን ጠቁመው፤ ዓባይና ቀይባህር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የሚያረጋግጡ መሠረቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
እንዲሁም በቀይባህር አቅራቢያ የሚታዩ ዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውድድሮች እና የባህር ላይ የደህንነት ስጋቶችን ማቃለል የሚያስችላት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ያሳዩትን አንድነት በቀይ ባህር ላይም መድገም እንዳለባቸው አመልክተዋል።