ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው በብዝሃ ህይወት እና ዘላቂ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ረገድ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በምርምር እንዲፈቱ እያገዘ ነው

ሮቤ፤ ነሐሴ 5/2018(ኢዜአ)፡- የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በብዝሃ ህይወት እና ዘላቂ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና እንክብካቤ ረገድ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በምርምር ተለይተው እንዲፈቱ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገለጸ። 

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የጎባ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት "ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሀሳብ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዛሬ አካሄደዋል።


 

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬት በየጊዜው ከሚያደርገው ተሳትፎ በተጓዳኝ በዘላቂ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ረገድ ሳይንሳዊ ምርምር እያካሄደ ይገኛል። 

ዩኒቨርሲቲው በተለይም በባሌ አካባቢ የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን በሳይንሳዊ ምርምር የማገዝ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጾዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱት ምርምሮች፣ ከችግኝ ተከላ ጋር ተያይዘው በአየር ንብረትና በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በጥናት ለመለየትና መፍትሔ ለመስጠት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የጎባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በንቲ ኦፍገሃ በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ዙሪያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሰሩት ሥራዎች የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን ገልጸው፤ በተለይም የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በመደረጋቸው ጠፍተው የነበሩ የዱር እንስሳትና ምንጮች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።


 

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት መካከል መምህር ኡመር መሐመድኑር፣ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ እንደ ዜጋ በየዓመቱ ከመሳተፍ ባሻገር ችግኞቹ ፀድቀው ለውጤት እንዲበቁም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ሥራው የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ለኢኮኖሚ ዕድገት መፍትሄ በሚሆን አግባብ መከናወን እንደሚገባውም እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በጎባ ክፍለ ከተማ ''ስራክ ጥብቅ ደን'' አካባቢ በተካሄደው መርሐ ግብር የደን፣ የመጠለያ፣ የእንስሳት መኖና ሌሎች ችግኞች መተከላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም