ቀጥታ፡

በክልሉ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ሥራዎች ውጤታማነትን እያሳደጉ ነው

ቡታጅራ፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ሥራዎች የኢንዱስትሪውን ውጤታማነት ይበልጥ እያሳደገው መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከ312 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ኢንዱስትሪዎች በቡታጅራ ከተማ ያስገነባቸውን የማምረቻ ሼዶች ዛሬ አስረክቧል።


 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ናትናኤል ሚሊዮን በዚሁ ወቅት፣ ኮርፖሬሽኑ የአምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ከማበረታታት ባለፈ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችን ጨምሮ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን በማስፋፋት ለሥራቸው ምቹ ሁኔታ እየፈጠረም ይገኛል።

በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ የግል ባለሀብቱን እና ሥራ አጥ ዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን ገልጸው፣ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካትም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ተችሏል ብለዋል።

በዛሬው እለትም ከ312 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 7 አምራች ኢንዱስትሪዎች ስምንት ሼዶች የተላላፉ መሆኑን ገልጸው፣ ኢንዱስትሪዎቹ ከ 387 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

አቶ ናትናኤል እንዳሉት፣ ኮርፖሬሽኑ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተለያየ መንገድ በመደገፍ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ተጨባጭ ውጤት ለማስቀጠል የጀመረውን ሥራ ያጠናክራል።

ዛሬ የማምረቻ ሼድ  ከተላለፈላቸው ኢንዱስትሪዎች መካከል በዱራሜ ከተማ የከምባታ ቡና ማቀነባበሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ ሰልፊሶ በሰጡት አስተያየት ኢንዱስትሪው 150 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ መቋቋሙን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅትም ከ150 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜአዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ በኮርፖሬሽኑ የተመቻቸላቸው የማምረቻ ሼድ ለስራቸው ውጤታማነት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው በሀደሮ ከተማ በዝንጅብል ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራው የሱዳስ ግሩፕ ሥራ አስኪያጅ አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው ኢንዱስትሪው በ70 ሚሊዮን ብር የመነሻ  ካፒታል ወደሥራ መግባቱን ተናግረዋል።


 

ኢንዱስትሪው ለ100 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የማምረቻ ሼዶችን ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማስተላለፍ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የክልል ከፍተኛ አመራሮችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም