ሀገራዊ ምክክሩ የሀገርን ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽዖ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የሀገርን ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽዖ ይኖረዋል
አምቦ፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ የሀገርን እድገት ለማፋጠን እና ዘላቂ ሰላምን እውን ያደርጋል ብለው እንደሚጠብቁ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች አስታወቁ።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር የማጠቃለያ ጉባዔ በማካሄድ ላይ ትገኛለች።
በምክክሩ የብዙሃን ድምፅ የሚሰማበት የተዛቡ የፖለቲካና የህብረተሰብ ተረኮች የሚታረሙበት እንዲሁም የጋራ የወደፊት ራዕይ የሚቃኝበት ታላቅ ሀገራዊ መድረክ እንደሆነም ይታመናል።
የአምቦ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች እንደገለጹት፤ ምክክሩ ቀደም ሲል በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በሌሎች ዘርፎች በዜጎች መካከል የነበሩ አለመግባባቶችንና የግጭት መንስኤዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ በቀለ ባይሳ፤ ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን በንግግር በመፍታትና የጋራ ሐሳቦችን በማጠናከር የሀገራቸውን ልማት ማፋጠን የሚችሉበት ዐውድ ላይ መድረሳቸውን ያሳያል ብለዋል።
ለዓመታት ቅሬታና ግጭት ሲፈጥሩ የቆዩ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄዎች በውይይት ሲፈቱ ሁሉም ዜጎች በአሸናፊነት ለሀገር እድገት የሚቆሙበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
አቶ በቀለ አክለውም፤ ችግሮችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በማምጣት መመካከር ለነበሩት ችግሮቻችን መፍትሄ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የመምከር ባህልን በህዝቡ ዘንድ ያሰርጻል፤ የተሻለች ሀገርንም ለትውልድ ያሻግራል ብለዋል።
ሌላኛው የከተማዋ የሀገር ሽማግሌና የምክክር ሂደቱ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ባይሳ ጆብር በበኩላቸው፤ ሂደቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
አቶ ፉፋ ቀቀባ የተባሉት የሀገር ሽማግሌ ደግሞ፤ ኢትዮጵያውያን የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት ሳይበግራቸው በፍቅርና በመከባበር ባህል ለዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም አጥፊና ከፋፋይ ጉዳዮችን በማስቀረት የጋራ ሀገራዊ ትርክቶችን ለመገንባት የሚያስችል የምክክር ሂደት መሆኑን ጠቁመዋል።
አካታች የሆነው ይህ ሀገራዊ ምክክር የሕዝቦችን ጥያቄ በውይይት የሚመልስ በመሆኑ፣ ሁሉም ዜጋ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ጥሪ በማቅረብ፤ እሳቸውም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።