በከተማው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል
ደብረ ብርሃን ፤ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች አፈጻጸም የግምገማ መድረክን እያካሄደ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በመድረኩ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
ከተከናወኑ ሥራዎች መካከልም በጤና፣ በትምህርት፣ በገቢ አሰባሰብና በቱሪዝም ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር ከኅብረተሰቡ ጋር በመናበብ ባከናወናቸው ተግባራት፣ በፓርቲና በመንግሥት ሥራዎች የተቀመጡ ግቦች በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወኑ ማስቻሉን ገልጸዋል።
እንዲሁም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት የሥራ ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ ለጠየቁ 228 አዳዲስ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸው፣ ለባለሀብቶቹም 70 ሄክታር መሬት መተላለፉን ጠቅሰዋል።
በከተማው እየተገነቡ የሚገኙ የኮሪደር ልማትና የአንድ መሶብ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትም በቀጣይ የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚያቃልል መልኩ እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማሻሻልም የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ ገበያው እንዲረጋጋ የማድረግ ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።
በ2019 በጀት ዓመትም የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎችን አቀናጅቶ በማከናወን የኅብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ጌታቸው፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የተለያዩ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ በከተማ አስተዳደሩ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆንና የአካባቢውን ሰላም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን ሆኖ በመጠበቁ በከተማው ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አስችሏል ብለዋል።
በውይይት መድረኩም የከተማ አስተዳደሩ፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።