በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሥራ ዕድል ፈጠራ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሥራ ዕድል ፈጠራ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል
ሆሳዕና፤ ነሀሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዜጎችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በእንጨትና ብረታብረት እንዲሁም በሌሎች መስኮች የሥራ ዕድል በመፍጠር የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተጀመሩ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል።
ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለ400 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ ከ379 ሺህ 430 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራውን ውጤታማ ለማድረግም በበጀት ዓመቱ ከ925 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ብደር መመቻቸቱን፣ 8 ሺህ 420 ሄክታር መሬት መቅረቡን እና 689 አዳዲስና ነባር ሼዶች ለኢንተርፕራይዞች እንዲተላለፉ መደረጉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል በጉራጌ ዞን እምድብር ከተማ ነዋሪ ወጣት ዳዊት ትዛዙ እንዳለው ከመንግስት ባገኘው የገንዘብ ብድር በቅመማ ቅመም፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ መሰማራቱን ጠቁሟል።
በአራት ሄክታር መሬት ላይ እያለማ ያለውን ቲማቲም ሽንኩርትና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መጀመሩንም ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅትም ከራሱ ባለፈ ለሌሎች ሥራ አጥ ወገኖች ጊዜያዊ ሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጿል።
በመንግስት ካገኘው የገንዘብ ብድር በተጨማሪ በተሰማራበት የእርሻ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግለትም ተናግሯል።
ሌላው በሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ወጣት ዳንኤል አሰፋ በበኩሉ በከተማው በሚገኘው ታዴ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረለት ገልጿል።
በዚህም በሚያገኘው ገቢ እራሱን ከማስተዳደሩ በተጨማሪ ነገ የራሱን ሥራ በመፍጠር ሕይወቱን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ራዕይ እንዲሰንቅ ማድረጉን ተናግሯል።