በኦሮሚያ ክልል የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ጅማ ፤ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ረሂማ ዩሱፍ አስታወቁ።
በጅማ ዞን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት እና ሌሎች የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ተጠናክረው እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለትም በዞኑ ማና እና ጎማ ወረዳዎች ለአቅመ ደካማ ወገኖች በበጎ ፈቃድ የተለያዩ ድጋፎች ተደርገዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ረሂማ ዩሱፍን ጨምሮ የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር እና ሌሎችም የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የተደረገው ድጋፍ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ሕይወት በዘላቂነት ለመቀየር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
ከተደረጉት ድጋፎች መካከል የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ፣ የምግብ ግብዓት፣ የንብ ቀፎዎች እና ዘመናዊ የኤክትሪክ ምጣድ ይገኙበታል።
ወይዘሮ ረሂማ በወቅቱ፤ በክልሉ በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ውስጥ የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሁሉም በያለበት በመተባበር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዞኑ ከ5 ሺህ 500 በላይ የአቅመ ደካሞችን ቤት ለማደስ ታቅዶ እስካሁን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መታደሳቸውን ተናግረዋል።
የተደረገው ድጋፍ የዕለት ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት ያለው መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ ድጋፉ የተደረገላቸው ወገኖች ሰርተው ሕይወታቸውን መለወጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በማና ወረዳ በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር እስካሁን ከ300 በላይ የሚሆኑ የአቅመ ደካሞች ቤቶች መጠገናቸውን የገለጹት ደግሞ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሰመሩዲን አህመድ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ የደም ልገሳ እና ሌሎችም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እገዛ ብቻ ሳይሆን እንደ ገዳ ስርዓት ነባር የመተሳሰብ እና የመደጋገፍ ባህላችን ነው ብለዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የማና ወረዳ ነዋሪዎቹ ወይዘሮ ፋጡማ አባገሮ እና ትዕግስት ጌታቸው፤ የተደረገላቸው ድጋፍ የዕለት ጉርስ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ህይወታቸውን የሚቀይር መሆኑ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በቀጣይ ሰርተው በመለወጥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሌሎችን እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል።