ቀጥታ፡

አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ምህዳር ለመገንባት ወሳኝ የሆነውን ብቁ የሰው ሃይል የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ምህዳር ለመገንባት ወሳኝ የሆነውን ብቁ የሰው ሃይል የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሂሚድ ገለጹ።

5ተኛው ዙር ብሄራዊ የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ የታዳጊዎች የስልጠና መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀምሯል።


 

መርሃ ግብሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሚያዘጋጀው ሲሆን በሳይበር ደህንነትና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ዝንባሌ ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ለማፍራት ያለመ ነው።

የሳይበር ደህንነት፣ሶፍትዌር ልማት፣ኮዲንግ፣ አቪዬሽን፣የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፎች በመርሃ ግብሩ ተካተዋል።

የሀርድ ዌር እና ሴኪዩሪቲ ዲዛይኖችን ማዘጋጀት የስልጠና መርሀ ግብር ሌላው የትኩረት ማዕከል ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤የኢትዮጵያን ዲጂታል ሽግግር ውጤታማ ለማድረግ የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ለዚህ ደግሞ በቁ የሰው ሃይል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሰው ሃይል የማፍራቱን ተግባር አጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀዋል።

የሰመር ካምፕ የስልጠና መርሃ ግብር የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ መርሃ ግብሩ የነገ የኢትዮጵያ ተስፋ የሆኑ ተተኪ ትውልድ በማፍራት ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የስልጠና መርሃ ግብሩ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ መጀመሩን አስታውሰው ፤ በአሁኑ ወቅት ስልጠናው በባህር ዳር፣ጅማ ፣ወላይታ ሶዶ፣ሀረማያ ዩንቨርስቲዎችን ጨምሮ በአስተዳደሩ ግቢ ውስጥ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እውን ለማድረግ የቴክኖሎጂ አቅሙ የተገነባ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የጀመረው ተተኪ ትውልድ የማፍራት ስራ የሚያስመሰግን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለመርሃ ግብሩ ስኬት ዩንቨርሲቲው የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

ሰልጣኞችም ኢትዮጵያን የማገልገል አደራ አለባቸሁ፤ለዚህ ደግሞ ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትላችሁ ተገቢውን ክህሎት ልትጨብጡ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም