የምክክር ጉባኤው በሀሳብ ብዝሃነት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ተስፋ ሰጪ ነው- ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው በሀሳብ ብዝሃነት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ተስፋ ሰጪ ነው- ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 5 /2018(ኢዜአ)፦የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን እያሳተፈ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ፣ የሀሳብ ብዝሃነትን በማንጸባረቅ ለጋራ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም መሠረት የሚጥል ተስፋ ሰጪ ሂደት መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንደተናገሩት፤ ምክክሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ማህበረሰቦች እኩል ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል በመስጠት አካታችነቱን እያረጋገጠ ነው።
ከተመካካሪዎቹ መካከል አባገዳ ለሜቻ ለማ እንደገለጹት፤ በምክክሩ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት እየቀረቡና እየዳበሩ ይገኛሉ።
በምክክሩ ሁሉም ተመካካሪ ሀሳቡን በነጻነት እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህም በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የጋራ መግባባት የተፈጠረባትና አንድነቷ የጸናች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው ተመካካሪ ባዬ በሬ በበኩላቸው፤ ምክክሩ ከአካታችነት አንጻር ሁሉንም የሚያሳትፍና የሀሳብ ብዝሃነት የሚንጸባረቅበት መሆኑን ገልጸዋል።
በምክክሩ ላይ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሀሳቦች እየቀረቡ መሆናቸውን ገልፀው ፤ ይህም የተሻለ ነገን መገንባት እንደሚቻል እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።
የምክክር ሂደቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በሚወክል መልኩ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አለሙ አሻግሬ (ዶ/ር) ናቸው።
ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በምክክር የመፍታት አዲስ ባህል መሆኑን ገልጸው፤ ሂደቱ ዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የምትሆን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።