ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን ለመኸር አዝመራ ከተዘጋጀው መሬት ከ106 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

አዶላ፣ ነሐሴ  5/2018(ኢዜአ) ፡-በጉጂ ዞን ለመኸር አዝመራ ከተዘጋጀው መሬት እስካሁን ከ106 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በተለያዩ  የሰብል ምርጥ ዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን በቆላማ፣ በደጋ እና በወይና ደጋ አየር ንብረቶች የተከፋፈለ በመሆኑ የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን ለማምረት አመቺ ተፈጥሮ አለው።

በዞኑ ከነሐሴ እስከ መስከረም አጋማሽ የዝናብና የዘር፣ እንዲሁም ከታኅሣሥ እስከ ጥር መጨረሻ የምርት ስብሰባ ወቅት ሲሆን፤ በመኽር ወቅት በብዛት ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ቦሎቄ እና ዘይት ነክ ሰብሎች ይጠቀሳሉ።


 

በዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ መንግሥቱ ሂርባዬ እንደገለጹት፤ ለተያዘው የመኸር አዝመራ 498 ሺሕ 778 ሄክታር መሬት በተለያዩ ምርጥ የሰብል ዘር በማልማት ከ13 ሚሊዮን 200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል።

በተያዘው የመኽር እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን መተግበርና ግብዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል። 

በዚህም መሠረት የሜካናይዜሽን እርሻን ማስፋፋት፣ በኩታገጠም የመሬት ዝግጅትና በመስመር የመዝራት ዘዴዎችን በመጠቀም ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመኽር ልማቱ እስከ አሁን በተደረገው እንቅስቃሴ፤ 119 ሺሕ 216 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 106 ሺሕ 159 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም  አሰራር በተለያዩ ምርጥ የሰብል ዘሮች መሸፈኑን አስታውቀዋል።

በዞኑ በመኽር አዝመራው ከሚለሙት የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች መካከል፤ በዋናነት እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ እና ቦለቄ ያሉ የእህልና የጥራጥሬ ሰብሎች ይጠቀሳሉ ብለዋል።

ከግብዓት አቅርቦት አንጻርም በዞኑ ለሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች 12 ሺሕ 429 ኩንታል ምርጥ ዘር እና 71 ሺሕ 600 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ማቅረብ መቻሉን አስታውቀዋል።

በእርሻው ተሳታፊ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል በዞኑ የአዶላ ሬዴ ወረዳ የደራርቱ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኔንቆ ዋሬ፤ ባለፈው የምርት ዘመን የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን በመተግበር ካለሙት የእርሻ መሬት የተሻለ ምርት መሰብሰባቸውን ያስታውሳሉ።

ካለፈው ዓመት ያገኙትን በጎ ተሞክሮ መሠረት በማድረግ፤ በዘንድሮው የመኽር እርሻ በኩታ ገጠም ለማልማት ካዘጋጁት ማሳ ከፍተኛ ምርት ለማግኘት አልመው በትጋት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማቴዎስ አዱላ በበኩላቸው፤ ለምርት ዘመኑ የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓቶች  በወቅቱና በበቂ ሁኔታ እንደቀረበላቸው አንስተው፣ የታቀደውን ምርትና ምርታማነት ለማሳካት የግብርና ባለሙያዎች በቅርበት ዕገዛ እያደረጉላቸው መሆኑን አክለዋል።

የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የሰብል ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የጠቆሙት አርሶ አደሩ፤ አሠራሩ አላስፈላጊ ወጪንና ጉልበትንም የሚቀንስ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም