ስልጠናው ከሳይንሳዊ እውቀት በተጨማሪ የስራ ተነሳሽነታችን የፈጠረ ነው -መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
ስልጠናው ከሳይንሳዊ እውቀት በተጨማሪ የስራ ተነሳሽነታችን የፈጠረ ነው -መምህራን
ባህር ዳር፤ ነሃሴ 5/2018(ኢዜአ)፡- የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው ሳይንሳዊ እውቀትና ክህሎትን ከማሳደግ ባሻገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ተነሳሽነትን ፈጥሮልናል ሲሉ በባህር ዳር ከተማ ስልጠና በመውሰድ ላይ ያሉ መምህራን ተናገሩ።
በባህር ዳር ከተማ እየተሰጠ ያለውን ስልጠና የሚከታተሉ መምህራን እንደገለጹት፤የክረምት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው እውቀትና ክህሎታቸውን በማሳደግ ከፍተኛ አቅም ፈጥሮላቸዋል።
ከሰልጣኞቹ መካከል መምህር ሀብታሙ ወንድሜነህ፣ስልጠናው በአብዛኛው ተግባር ተኮር በመሆኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ "ተማሪዎችን በአካባቢያቸው ከሚገኙ ተጨባጭና በሚዳሰሱ ቁሳቁሶች ላይ ተመስርቶ በማስተማር የፈጠራ ችሎታቸውን ማዳበር እንደሚገባ እውቀት አግኝቻለሁ" ብለዋል።
የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት ነጻነት አለምነህ በበኩላቸው ፤ ስልጠናው ለተማሪዎች አራቱን መሰረታዊ የቋንቋ ክህሎቶች በቀላሉ ለማስተላለፍ የሚያስችል ዘዴና እውቀት እንዳስጨበጣቸው ተናግረዋል።
የነበሩ ክፍተቶችን በመለየትና የትምህርት እቅድ አወጣጥን የተሻለ በማድረግ የመማር-ማስተማር ሂደቱን የተቃና ለማድረግ እንደረዳቸውም ነው የጠቆሙት።
የመምህራን አቅም መጎልበት ለትውልድ ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ስልጠናውን በከፍተኛ ፍላጎት እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የአጠቃላይ ሳይንስ መምህርቷ ወርቃለም መኮንን ፤በስልጠናው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አዳዲስ የማስተማር ዘዴዎችን መቅሰማቸውን ጠቁመዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ትበይን ባንቲሁን፤ የትምህርት ጥራት መሰረት ለሆኑት መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና መስጠት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በክረምቱ የተመደበውን ኮታ ሙሉ በሙሉ በመጠቀም መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች እንዲሰለጥኑ መደረጉን ተናግረዋል።
ስልጠናው በዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚሰጥ በመሆኑ መምህራን በተነቃቃ መንፈስ ተማሪዎቻቸውን እንዲቀበሉና የተሻለ የመማር-ማስተማር ስርአት እንዲዘረጉ ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአማራ ክልል በክረምቱ ወቅት ከ10 ሺህ በላይ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በ11 የስልጠና ማዕከላት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።