ሪፈራል ሆስፒታሉ በሚሰጠው ነፃ የምርመራና የህክምና አገልግሎት በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሪፈራል ሆስፒታሉ በሚሰጠው ነፃ የምርመራና የህክምና አገልግሎት በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው
ሮቤ፤ ነሐሴ 5/2018(ኢዜአ)፡- በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ነፃ የምርመራና ህክምና አገልግሎቶች በመስጠት ላይ ይገኛል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በክረምት ወራት በሚያካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አማካኝነት ለአካባቢው ህብረተሰብ ነፃ የምርመራ፣ የህክምና እና የቀዶ ጥገና አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።
በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ሀላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ፣ የህክምና ወጪን መሸፈን ለማይችሉ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ትልቅ እፎይታን ፈጥሯል።
የሪፈራል ሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐመድአማን ማማ ለኢዜአ እንዳሉት ሪፈራል ሆስፒታሉ የተሻለ የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው።
በተለይም በመደበኛነት ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ባሻገር በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለያዩ ችግሮች ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ ያልቻሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
አገልግሎቱ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና ራሳቸውን ሳያውቁ ለተለያዩ በሽታዎች የተጋለጡ ሰዎች ተገቢውን ህክምና እንዲከታተሉ የማስቻል ዓላማ ማድረጉንም አክለዋል።
በዚህም በክረምቱ ወቅት ከ120 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ እስከ አሁን 150 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንና ሥራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተሰጡ ከሚገኙት ነፃ የምርመራና የበሽታ ልየታ አገልግሎቶች በተጓዳኝ በመደበኛው የህክምና አገልግሎት ወቅት የቀዶ ህክምና ወረፋ ሲጠባበቁ የነበሩ ህሙማን ጭምር የሚስተናገዱበት አሰራር መመቻቸቱ መርሃግብሩን ልዩ ያደርገዋል።
በዩኒቨርሲቲው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጤና ትምህርትና ህክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ አቤል በልሁ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው የምርመራና የህክምና አገልግሎት በተጓዳኝ በበሽታ ተጋላጭነትና መተላለፊያ መንገዶቹ ላይ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
"በጎነት ለጤናችን'' በሚል መርህ እንደ ሀገር በተጀመረው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጤና ባሻገር የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ እና ሌሎች በጎ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አውስተዋል።
በሆስፒታሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘመቻው አስተባባሪ ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ሰለሞን ክፍሌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የህክምና ባለሙያዎቹ ቡድን ከሚሰጡት አገልግሎት መካከል የደም ግፊት፣ ኤች.አይ.ቪ፣ የስኳር በሽታ፣ የጡት ካንሰር፣ የጉበት በሽታ፣ የዓይን ምርመራና የሌሎች በሽታዎች ልየታና ህክምና ይገኙበታል።
የሕክምና ቡድኑ በሚኖረው ቆይታ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን የመለየትና የምርመራና የህክምና አገልግሎት ከመስጠት በተጓዳኝ ተጨማሪ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ህሙማን በመለየት ለተጨማሪ ምርመራና ህክምና ከሆስፒታሉ ጋር የማገናኘት ስራ እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡
ከነፃ ህክምናው ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ አልፊያ ሁሴን እንዳሉት ሆስፒታሉ በጀመረው ዘመቻ በቀላሉ ህክምና በማግኘት ያሉበት የጤና ደረጃ ለማወቅ አስችሏቸዋል።
አቶ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው የህክምና ባለሙያዎች በነፃ በሰጡት የምርመራ አገልግሎት ከበሽታ ስጋት ነፃ በመሆናቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በአገልግሎቱ ሰዎች በበሽታ ከመጎዳታቸው በፊት ራሳቸውን አስቀድመው እንዲያውቁ ያገዛቸው በመሆኑም ተቋሙን አመስግናዋል።