በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የተጀመሩ ውጤታማ የለውጥ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የተጀመሩ ውጤታማ የለውጥ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የተጀመሩ ውጤታማ የለውጥ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው ገለፁ።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ክንውን እና የ2019 የትኩረት አቅጣጫዎች የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።
ፕሬዝዳንቱ አቶ ዓለምአንተ አግደው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የፍርድ ቤቶችን አሰራር በቴክኖሎጂ ታግዞ በማዘመን በኩል ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይ ቀደም ሲል ማህበረሰቡ በአሰራር ዙሪያ ያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ባለፋት ሦስት ዓመታት የፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል።
በተቀናጀ አግባብ በተሰሩ የለውጥ የአሰራር ማሻሻያዎች፣ የዲጅታላይዜሽን ትግበራዎች እና የተቋማት ግንባታዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዚህም በፍርድ ቤቶች በሚታዩ መዝገቦች ቁጥር፣ የዳኝነት አሰጣጥ ጥራትና ፍጥነት ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን አረጋግጠዋል።
መደበኛ ፍርድ ቤቶች ግልፅና ተጠያቂነት ባለው መንገድ መዳኘት ያስቻለ የቴክኖሎጂ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ማዘመን እንደተቻለም ተናግረዋል።
እንዲሁም አማራጭ የዳኝነት መስጫ ማዕከላትን ተደራሽ በማድረግም ዜጎች በአቅራቢያቸው ሆነው ያለምንም ወጭና ድካም የዳኝነት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አሰገንዝበዋል።
ፍርድ ቤቶች ገለልተኝነትና ነፃነታቸውን በጠበቀ መንገድ ከተቋማት ጋር በጠንካራ ትብብርና ቅንጅት እየሰሩ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የዳኝነትና የፍትህ አሰጣጡን በማዘመንና ተደራሽነታቸውን በማሳደግ ማህበረሰቡ የበለጠ የሚተማመንባቸው በማድረግ በኩል የተጀመሩ የለውጥና የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ዙሪያ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል፤ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡም እውቅናም እንደሚሰጥ ነው የተገለፀው።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ስራ እና የዲጅታላይዜሽን ትግበራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት መጎብኘታቸው ይታወሳል።