ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው የሕዝብ አንድነትን የሚያጠናክር ነው-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 5 /2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሕዝብ አንድነትን የሚያጠናክርና ኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን የሚያስችል የጋራ መግባባት ይገነባል የሚል ተስፋ አለን ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

በጉባኤውም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች፣በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፣ የምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያውያን መካከል የጋራ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ወሳኝ መንገድ እንደሆነ ከፍተኛ እምነት አላቸው።

የምክክር ሂደቱ የሀገርን አንድነት ለማጠናከር፣ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማሳደግ የሚያስችል የጋራ መግባባት እንደሚፈጥር ትልቅ ተስፋ የጣሉበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ሮቤል ብርሃኑ፣ ሀገራዊ ምክክር በዜጎች መካከል የጋራ መግባባትን የሚገነባ አዋጭና ስልጡን አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገራዊ ችግሮች ዙሪያ በአንድ ጣሪያ ሥር ምክክር ሲደረግ፣በመሠረታዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባትን ለመገንባት የሚያስችል ወሳኝ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በፖለቲካው መስክ መግባባትን በመፍጠር የሀገርን የኢኮኖሚ አቅም የሚገነባ የተረጋጋ የልማት ሥራን ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤም የኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝብ አንድነትን የሚያጠናክር የጋራ መግባባት የሚገነባ አዎንታዊ ምክረ ሐሳቦች የሚፈልቁበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ኃይሌ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ የአንድ ሀገር ዜጎች በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር የምክክር ሐሳብ በመወጠን መሰባሰባቸው በራሱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

ከዚህ ታሪካዊ መድረክ በኋላም የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያሳልጥ የጋራ መግባባትን በመገንባት፣ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ መሪ ሀገር ለመሆን የሚያስችላትን አቅም እንደምትፈጥር እምነታቸውን ገልጸዋል።

የምክክር ጉባኤው አካታችነት በዜጎች መካከል የጋራ መግባባትን በመገንባት የሕዝብ አንድነትን ይበልጥ ያጠናክራል የሚል ተስፋ አለኝ ያሉት ደግሞ ያደታ ጉደታ ናቸው።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ አልማዝ ታምራት በበኩላቸው፣ የምክክር ጉባኤው በዜጎች መካከል ጠንካራ መግባባት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት መሠረት የሚጥል የጋራ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የመዲናዋ ነዋሪ አስቻለው በርጋ እንዲሁ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር የሚያግዝ ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።

አቶ ገረመው ደበበ በበኩላቸው፣ የሀገራዊ ምክክሩ ውጤትም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን የጋራ መግባባት ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም