ቀጥታ፡

የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቃና ለከተማዋም ተጨማሪ ድምቀት ነው

አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ)፡-በገበታ ለትውልድ መርሐግብር የተገነባው የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቃና ለከተማዋም ተጨማሪ ድምቀት መሆኑ ተገለጸ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የተገነባውና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነው አርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት በቅርቡ መመረቁ ይታወቃል።

ኢዜአ ያነጋጋራቸው የአርባ ምንጭ ከተማ ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ደስታ ደምበላ እንደገለጹት ሪዞርቱ ለአካባቢው ብሎም ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ነው። 


 

ሪዞርቱ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል መሆኑንም ጠቅሰው፣ የቱሪዝምና የአገልግሎት ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር አስተዋጾ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ሪዞርቱ የተገነባበት ቦታ ለቱሪዝም ምቹ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደስታ፣ በተለይ በዓባያ ሐይቅ ላይ የተገነባው ተንሳፋፊ ሬስቶራንት የተለየ በመሆኑ የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባል ብለዋል ። 

እንደሃላፊው ገለጻ የአካባቢውን የቱሪዝም ፀጋዎች ይበልጥ እንዲታወቁ በማድረግ በኩልም ፋይዳው የጎላ ሲሆን ሀገራዊ ጠቀሜታም ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪው አፈወርቅ አለማየሁ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ያስገነቧቸው ፕሮጀክቶች የሀገርን ገጽታ በመሰረታዊነት የቀየሩ ናቸው። 


 

ሪዞርቱ በአርባ ምንጭና አካባቢው የሚገኘውን የሸማ ጥበብ፣ የባህል፣ የምግብና የአልባሳት ሥራዎችን ለማስተዋወቅና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ምቹ ዕድል ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል።

በግንባታው ሂደት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰው፣ በቀጣይም ለዜጎች በቋሚና በጊዜያዊነት ተጨማሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ሙና ዮሐንስ ሪዞርቱ የከተማዋን ውበት አጉልቶ የሚያወጣ ተጨማሪ ፀጋ ነው ሲሉ ገልጸዋል።


 

ወጣት ታምራት በርገኔ በበኩሉ ሪዞርቱ የአርባ ምንጭ ከተማን ገጽታ ይበልጥ ከማድመቅ ባለፈ ቱሪስትን በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፆ፣ ይህም ለከተማዋና ለሀገር እድገት የሚኖረው አበርክቶ የጎላ ነው ብሏል።


 

አስተያየት ሰጪዎቹ  በአርባ ምንጭና አካባቢው ሰፊ የቱሪዝም አቅም በመኖሩ ሪዞርቱ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ቱሪስቶችና እንግዶች ምቹ ማረፊያ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የተመረቀው የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋፋት ባለፈ የሀገር የኢኮኖሚ አቅምን ከፍ ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው።

ሪዞርቱ ከ1ሺህ 300 በላይ ሰዎችን የሚያስተናግድ የስብሰባ አዳራሽና በሐይቅ ላይ የተገነባ ልዩ ተንሳፋፊ ሬስቶራንትን ያካተተ እንደሆነም በወቅቱ ተመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም "ሪዞርቱ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማስፋፋት ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረኮች ማዕከል የማድረግ ራዕያችንን ያጠናክራል፤ ለአካባቢውም ማህበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል" ሲሉ በወቅቱ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም