ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የተደረጉ ድጋፎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል

ሐረር ፤ነሐሴ 5/2018 (ኢዜአ) ፡-በሐረሪ ክልል የኢንዱስትሪውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማጉላት የተደረጉ ድጋፎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገባቸውን የክልሉ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ እስማኤል ዩሱፍ ገለፁ።

በክልሉ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ወጣቶች ተናግረዋል።


 

የክልሉ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ እስማኤል ዩሱፍ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ በክልሉ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት 231 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግም የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ ድጋፍና ክትትል መጠናከሩን ተናግረዋል።


 

ይህም የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ፣ ከ49 ሺህ ቶን በላይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት 60 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ማደግ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማስቻሉንም ተናግረዋል።

በቀጣይም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በተለይ የኮንስትራክሽን፣ የምግብና መጠጥ፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶችና ሌሎች ዘርፎችን የማስፋፋትና የማዘመን ሥራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።


 

በክልሉ በተደረገላቸው ድጋፍ ውጤታማ ከሆኑ ኢንዱስትሪዎች መካከል የታቲ የከረጢትና ጫማ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዑመር መሐመድ እንዳሉት፤ ፋብሪካው ፌስታልን ከማምረት ወጥቶ ተኪ የሆኑ የከረጢትና የጫማ ምርቶችን ማምረት መጀመሩን ተናግረዋል።

ይህም የማምረት አቅሙን በማሳደግ በገበያ ተወዳዳሪ ከመሆን አልፎ፣ ለአገር እድገት ያለውን አበርክቶ በማሳደግ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።


 

በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ በተፈጠረለት የሥራ እድል ተጠቃሚ በመሆኑ ራሱንና ቤተሰቡን ከመደገፍ ባለፈ የቴክኖሎጂ ክህሎቱን እያዳበረ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት መሐመድ ዙቤር ነው።



በክልሉ ኢንዱስትሪ ዞን በአልባሳት ማምረት ላይ በተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ጽዮን ሻውል በበኩሏ፤ የተገኘው የሥራ እድል ቤተሰቧን ለማስተዳደር እንዳገዛት ተናግራለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም