ኢትዮጵያን ማስቀደም፡ሀገራዊ ምክክሩና የዜጎች ዘላቂ መግባባት የመፍጠር ቁርጠኝነት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ማስቀደም፡ሀገራዊ ምክክሩና የዜጎች ዘላቂ መግባባት የመፍጠር ቁርጠኝነት
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመመካከር ዘላቂ መግባባት ላይ ለመድረስ ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳየው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በዜጎች የነቃ ተሳትፎ መካሄዱን ቀጥሏል።
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው ይህ ታሪካዊ ጉባኤ፣ በኢትዮጵያ ዘመናት የተሻገሩ ውስብስብ ችግሮችንና ልዩነቶችን በሰለጠነ ውይይት የመፍታት አዲስ ባህል እየገነባ ይገኛል።
ተመካካሪዎች በስምንት አጀንዳዎች በመካከር ላይ ይገኛሉ።
አጀንዳዎቹ የተለዩት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ ነው።
ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የቀረቡት ስምንቱ አጀንዳዎች ከኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ፣ ቅሬታ፣ ፍላጎት፣ ተስፋና ስጋት የተቀዱ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 በተሰጠው ስልጣን መሰረት፣ የህዝብን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያረጋገጠና "ከታች ወደ ላይ" የሚለውን ስልት የተከተለ አካታችና ሁሉን አቀፍ ስራ ማከናወኑን አስታውቀዋል።
የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ እንዲሁም የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስናና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ሰላም ግንባታ ምክክር እየተደረገባቸው ያሉ አጀንዳዎች ናቸው።
የሕዝቦችን አሰባሳቢ እሴቶች ለማጠናከርና የተራራቁ ትርክቶችን ወደ አንድነት ለማምጣት ያለመው ይህ የምክክር ሂደት፣በአሁኑ ወቅት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ከነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ከስልታዊ ቡድኖች የቀረቡ የአጀንዳ ምክረ-ሃሳቦች ተቀናጅተው ለስራ ቡድኖች መቅረብ የጀመሩ ሲሆን፣ምክረ ሀሳቦቹን የማቅረብ ሂደት ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህም በተጠናቀሩት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ያተኮረ ሰፊ ውይይት ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ነው።
በእያንዳንዱ 500 አባላት ባሉት 8 የስራ ቡድኖች ውስጥ ከተመረጡ 30 ተወካዮች የቀረቡት እነዚህ ሃሳቦች፣ ወደ አካታችና የመጨረሻ ምክረ-ሃሳብነት እንዲያድጉ በጥልቀት እየመረመሩ ይገኛሉ።
በጉባኤው ላይ 4000 በቀጥታ የሚሳተፉ ተመካካሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ እነዚህም በስምንት ተመካካሪ ቡድኖች ተከፋፍለው በስምንት ቁልፍ የምክክር አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመወያየት ላይ ይገኛሉ።
ሂደቱን በስልትና በስርዓት ለመምራት 16 ስልታዊ ቡድኖች፣160 አመካካሪዎች፣ 158 ቃለ-ጉባኤ ያዦች እንዲሁም የሙያ ድጋፍ የሚሰጡ 80 የባለሙያዎች ቡድን (Panel of Experts) ተመድበው በቅንጅት እየሰሩ ነው።
በተጨማሪም የሁሉንም ወገን ድምፅ ለማካተት ሲባል 336 የክልልና የፌዴራል ተወካዮች በሂደቱ ላይ በነቃ ሁኔታ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
ይህ ምክክር ዜጎች ከግል፣ከቡድን ወይም ከአካባቢያዊ እሳቤዎች ሙሉ በሙሉ በመውጣት ኢትዮጵያን በማስቀደም እየተካሄደ ይገኛል።
ሕብረተሰቡ በየደረጃው የሚያደርገው የነቃ፣ግልጽና አካታች ተሳትፎ፣በኢትዮጵያ የጋራ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህልን ከማሳደጉም በላይ የዜጎችን እውነተኛ ባለቤትነት ያረጋገጠ ነው።
ይህ ሀገራዊ ምክክር ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ወንድማማችነትና የጋራ ዕድገት ጽኑ መሰረት የሚጥል ታሪካዊ ክስተት ነው።
ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሙሉ ነፃነትና ተስፋ ተወያይተው የጋራ መግባባት በመፍጠር፣ ሀገራቸውን ወደ ተሻለ የልማትና የስልጣኔ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችላቸውን አዲስ ተስፋ በጋራ በመገንባት ላይ ይገኛሉ።