ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር አባል ሆነች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር (World Boxing) ባወጣው መረጃ መሰረት የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ኢትዮጵያን ጨምሮ የስድስት አገራትን የአባልነት ጥያቄ ማፅደቁን አሳውቋል።

ይህንኑ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ እያሱ ወሰን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ማህበሩን በመቀላቀሏ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

አክለውም፣ ይህ ለኢትዮጵያ የኩራት ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ የአፍሪካ የቦክስ ቤተሰብ ለሁላችንም የደስታና የክብር ወቅት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም በአፍሪካ ስፖርቱን የሚያጠናክር እያንዳንዱ እርምጃ ለሁሉም ድል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ አዲሱ ምዕራፍ ለአፍሪካ ቦክስ ታላላቅ እድሎችንና ስኬቶችን ይዞ እንደሚመጣም ያላቸውን ምኞት መግለጻቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ቻድ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ የመን እና ኩዌት ሌሎች የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር አባል የሆኑ ሀገራት ናቸው።

የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር (World Boxing) የተቋቋመው እ.ኤ.አ. አፕሪል 2023 ነው።
ማህበሩ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የቀድሞው ዓለም አቀፍ የቦክስ ማህበር (IBA) የአሰራር እና የሙስና ችግሮች ስለነበሩበት፣ ቦክስ በኦሊምፒክ ስፖርትነት የመቀጠል እድሉን ለማስጠበቅ በሚል ዓላማ ነው።

ዋና መስሪያ ቤቱን በስዊዘርላንድ ያደረገው የዓለም አቀፉ የቦክስ ማህበር (World Boxing) ዛሬ አባልነታቸው ተቀባይነት ያገኙትን ጨምሮ 168 አባል ሀገራት በስሩ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም