ቀጥታ፡

በዘላቂ ሰላምና ልማት ስራዎች ሚናችንን እናጠናክራለን-የመንግስት ሰራተኞች

ገንዳውኃ፣ ነሃሴ 4/2018 (ኢዜአ):- ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚከናወኑ ተግባራት ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።

የከተማው አስተዳደር ከመንግስት ሠራተኞች ጋር በሰላም፣ ጸጥታ እና በልማት ስራዎች ዙሪያ ምክክር  አካሂዷል። 

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የመንግስት ሰራተኞች በከተማው በሚከናወኑ በዘላቂ ሰላምና ልማት ስራዎች ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

ከሰራተኞች መካከል አቶ በረከት ገብሬ እንደገለጹት፣ ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥ ለልማት ስራዎች መፋጠን ወሳኝ ነው ።

ሰላምን በዘላቂነት በማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ዳር ለማድረስ በሚከናወኑ ተግባራት ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ አመልክተዋል ።

"የመንግስት ሰራተኛው የህብረተሰቡ ግንባር ቀደም አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን፣ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ እና የጸጥታ ስጋቶችን ቀድሞ በመከላከል ረገድ አርአያነታችንን ማሳየት አለብን" ብለዋል። 

ከድጃ ሙሳ በበኩላቸው፣ የህዝቡን የአገልግሎት ፍላጎት በታማኝነትና በጥራት ማሟላት ለሰላም መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል። 

"በየመሥሪያ ቤታችን ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ​አበርክቷችንን እናጠናክራለን ብለዋል ።


 

​የገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ ተወካይ አቶ አዳነ ሀሰን በበኩላቸው፣ በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሰራተኛው ተነሳሽነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። 

​የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በየደረጃው በመፍታት፣ ሰላምን የሚያጽኑና የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያፋጥኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።


 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በወቅቱ  እንዳሉት፣ የመንግስት ሰራተኛው የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎችን ግንባር ቀደም መሪ ሆኖ ሊፈፅም ይገባል።

በተለይም ሰላምን በዘላቂነት የማረጋገጥ ስራ የሁሉም መሰረት መሆኑን አመልክተዋል ።

​ሰራተኛው ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት በመስራት የሰላም አምባሳደር ሊሆን እንደሚገባ እና ለአካባቢው ደህንነት መጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም