የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፦የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በኦዲት ጥራት የግምገማ ውጤቶች ዙሪያ ከኦዲት ባለሙያዎችና ባለድርሻ ተቋማት ጋር ተወያይቷል።
የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ውብእሸት ታደለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኦዲተሮች የሒሳብና የኦዲት ሪፖርቶችን ጥራት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ የሙያ ደረጃዎችንና የሥነ-ምግባር መርሆዎችን በጥብቅ ክትትል ነጻና ገለልተኛነት ሆነው ሊሰሩ ይገባል።
በግምገማው የታዩ የኦዲት ጥራት ክፍተቶችን ለመሙላት የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማስፋፋትና የሙያ ደረጃዎችን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑም አስገንዝበዋል።
የቦርዱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር በበኩላቸው፤ ጥራት ያለው የኦዲት ሪፖርት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የታክስ ሥርዓቱን በብቃት ለማስኬድና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ካፒታል ገበያ እየተሸጋገረች በመሆኑም ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የኦዲት ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ኦዲተሮች ለሒሳብ አያያዝና ኦዲት ሪፖርቶች ጥራት መጠበቅ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውጭ ኦዲተሮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ጌታነህ፤ የኦዲት ድርጅቶች የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን መፈተሽና ክፍተት ያለባቸውን ማጠናከር የኦዲት ጥራትን ለማሻሻል ቁልፍ ነው ብለዋል።
የኮከብና መልካሙ ኦዲት አድራጊ ድርጅት ተወካይ ኮከብ ሞገስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአካውንቲንግ ትምህርት ከንድፈ ሀሳብ ባሻገር የተግባር ልምምድን ያካተተ እንዲሆን በማድረግ ብቁ የሒሳብና የኦዲት ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ውይይቱም በኦዲት ጥራት የታዩ ክፍተቶችን በመለየት የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።