መሶብ የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ለአፍሪካ ሀገራትም ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ለአፍሪካ ሀገራትም ያግዛል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ከፍተኛ ተሞክሮ የሚወስዱበት መሆኑን የኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አለማየሁ ገለጹ።
የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎትን ጎብኝተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ለጎብኚዎች በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓትን እንዲገነቡ ያግዛል።
የመንግሥት አገልግሎቶች በተለያዩ ተቋማት ተበታትነው መሰጠታቸው ዜጎች ለአገልግሎት ብዙ ተቋማት ጋር እንዲሄዱ ከሚያደርጉ ችግሮች ዋነኛው ነበር ብለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት መሶብ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትንና አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በማቀናጀት የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥን በተግባር እያስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል።
የመሶብ አገልግሎት ከአንድ ማዕከል አገልግሎት በመነሳት ወደ ተንቀሳቃሽና የቤት ለቤት አገልግሎት እንዲሁም ወደ ዲጂታል መድረክ መስፋፋቱንም አስረድተዋል።
በተለይም “ዩኒፋይድ መሶብ” የተሰኘው የኦንላይን መድረክ ዜጎች በሞባይል ስልካቸው የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመሶብ የዲጂታል አገልግሎት ልምድን ከኢትዮጵያ ውጭ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በቀጣይ ከጅቡቲ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኬንያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ዙሪያ ትስስር በመፍጠር የአህጉራዊ ዲጂታል ሥርዓት መገንባት የመሶብ ራዕይ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዘርፉ የኢትዮጵያን ልምድ ለአፍሪካ ሀገራት ማካፈል የሚያስችል መድረክ ለመሆን እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በፌዴራል መሶብ ዋና ማዕከል የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።