በክልሉ በንግድና በገቢ ተቋማት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የተጀመረው ቅንጅታዊ ሥራ ይጠናከራል-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በንግድና በገቢ ተቋማት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የተጀመረው ቅንጅታዊ ሥራ ይጠናከራል-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ሆሳዕና፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በንግድና በገቢ ተቋማት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በቅንጅት የሚሰራው ሥራ እንደሚጠናከር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።
በክልሉ ገቢዎች እና ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች በህገ ወጥ የንግድ ቁጥጥር፣ ገበያ ማረጋጋትና የታክስ ተገዥነትን ማረጋገጥ አስመልክቶ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር) በመድረኩ ማጠቃለያ እንዳሉት በክልሉ በንግድ እና በገቢ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን በቅንጅት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በተለይ በንግድ ሥርዓቱ የሚስተዋል ህገወጥነትን ለመከላከል በዘርፉ የወጡ ደንብና መመሪያዎችን ከሚያስፈጽሙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት የሚሰራው ሥራ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
በዚህም ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ የሚከናወኑ ህገወጥ ተግባራትን በመቆጣጠር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
በተጨማሪም ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠልና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሚጠናከሩ ነው እንዳሻው (ዶ/ር) የገለጹት።
ለዚህም ገቢን በአግባቡ የመሰበሰብ ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከደረሰኝ ገቢ አሰባሰብ ጋር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ ይሰራል ብለዋል።
በዚህ ረገድ አመራሩ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የህዝብን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሊተጋ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሀላፊ ባዩሽ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ በንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ላይ በተለያየ መንገድ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት አገልግሎቱን የማዘመን ሥራ እየተሰራ ነው።
በገበያ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት አምራቹንና ሸማቹን የሚያገናኙ ከ100 በላይ ገበያዎችና ሌሎች መደበኛ የግብይት ማዕከላት ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ አሰራሮችን በማረም ረገድ የተጀመሩ ተግባራትን ለማጠናከርም ቅንጅታዊ ሥራው እንደሚጠናከር ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በበጀት ዓመቱ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ከማህበረሰብ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ቀመሪያ ረሻድ ናቸው፡፡
ገቢን በአግባቡ የመስበሰብ ሂደቱን የሚያስተጓጉሉ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከደረሰኝ ገቢ አሰባሰብ ጋር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ ይጠናራል ብለዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ሀላፊ ኮሚሽነር አብርሃም ቲርካሶ በበኩላቸው በክልሉ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና የኮንትሮባንድ ዝውውርን ለመከላከል እየተሰራ ነው።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲታረሙ ከሚሽኑ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ህግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።