ቀጥታ፡

የኮደሮች ኢኒሼቲቭ፡ የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታና የወጣቶች ብሩህ መፃኢ ዕድል

በሙሴ መለሰ
 
ኢትዮጵያ በዲጂታሉ ዓለም ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እና የወጣቶችን ክህሎት ለማልማት ያለመው የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ  በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል።
 
ይህ ኢኒሼቲቭ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል በተደረገ ትብብር የተዘጋጀ  ሀገራዊ የዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮጀክት ነው።
 
ዋና ዓላማውም ወጣቶች በዲጂታሉ ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈለጉ የቴክኖሎጂ ክህሎቶችን እንዲጨብጡ ማስቻል ነው።
 
የስልጠናው መርሃ ግብር በኦንላይን ”Udacity” በተሰኘ ዓለም  የትምህርት መድረክ በኩል የሚሰጥ ሲሆን፣ በዌብ ዲቨሎፕመንት፣ በዳታ አናሊቲክስ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዋና ዋና ዘርፎች የተከፈለ ነው።
 
ከእነዚህም ጎን ለጎን የንግድና ሥራ ፈጠራ እንዲሁም የመሪነት ክህሎት አጫጭር ስልጠናዎች ተካተዋል።
 
እያንዳንዱ ኮርስ በግል ፍጥነት የሚወሰድ ሆኖ በአማካይ ከ6 እስከ 7 ሳምንታት የሚወስድ ሲሆን፣ ስልጠናውን በጥሩ ሁኔታ ላጠናቀቁ ሰልጣኞች ሙሉ በሙሉ በነፃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የ’Udacity’ እና የኢኒሼቲቩ ይፋዊ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይሰጣል።
 
በዚህ ፕሮግራም ላይ ዕድሜው ከ13 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የቀደመ የኮዲንግ እውቀት ሳይጠይቀው መመዝገብ ይችላል።
 
ለመማር የሚያስፈልጉት ነገሮች የኢንተርኔት ግንኙነት ያለው ኮምፒውተር ወይም ስማርትፎን ብቻ ሲሆኑ፣ ምዝገባውም በይፋዊው 5millioncoders.gov.et ድህረ ገጽ በኩል ይከናወናል።
 
የኢኒሼቲቩ የመጨረሻ ግቦች ሀገሪቱን በምስራቅ አፍሪካ እና በመላው አህጉር ውስጥ የቴክኖሎጂ ማዕከል ማድረግ እና የዲጂታል ስትራቴጂዎችን ማሳካት ናቸው።
 
በተጨማሪም ሰልጣኞች በሀገር ውስጥና በውጭ ድርጅቶች እንዲቀጠሩ፣ ከቤት ሳይወጡ በዶላር የሚከፍሉ የርቀት ስራዎችን እንዲሰሩ እና የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ስታርታፕ እንዲመሰርቱ መንገድ ይከፍታል።
 
በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚታየውን የክህሎት እጥረት በመሙላትና ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት የወጣቶችን ተወዳዳሪነትና በራስ የመተማመን አቅም ያሳድጋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት ሀገራዊ ጥሪ፣ ይህ ክረምት በከንቱ እንዲያልፍ ሳይፈቀድ ወጣቶች በነጻ የሚሰጠውንና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን ትምህርት እንዲወስዱ አሳስበዋል።
 
አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ቀድመው የወሰኑ በመሆናቸው፣ ሌሎችም ይህንን እድል በመጠቀም የክረምቱ ወቅት ከመጠናቀቁ በፊት የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ ሰባት ሚሊዮን ለማድረስ የቀረበውን ጥሪ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
 
ይህንን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተናጋጅነት የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።
 
ዝግጅቱ የዘርፉን መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎችን፣ የምስክር ወረቀት ያላቸውን የኢኒሼቲቩን ተመራቂዎች እና ወጣት ባለሙያዎችን በአንድነት ያገናኘ ሲሆን፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ባተኮረ የኤግዚቢሽን ጉብኝት ተጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም የመክፈቻ ንግግር ቀጥሏል።
 
ኃላፊዋ የወጣቶች የቴክኒክና የዲጂታል ክህሎት ብቃት ወሳኝ ሀገራዊ ሀብት መሆኑን ገልጸው፣ የኮደሮችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ የቀረበውን ጥሪ ተግባራዊነት አረጋግጠዋል።
 
ቀጥሎ በተካሄደው የፓናል ውይይት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር አብዮት ባዩ፣ የጊሮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቤተልሔም ደሴ፣ እንዲሁም የኢኒሼቲቩ ምሩቃን የሆኑት አዝመራው ታደሰ እና የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ማኅሌት ሥዩም ልምዳቸውንና እይታቸውን አካፍለዋል።
 
ፓናሊስቶቹ ወጣቶች ክህሎታቸውን ያለማቋረጥ እንዲያሳድጉ እና በኢትዮጵያ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ዕድገት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ያበረታቱ ሲሆን፣ መርሃ ግብሩም የኢኒሼቲቩን ከፍተኛ ሀገራዊ ሚና በድጋሚ ያረጋገጠ ሆኖ ማለፉን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።
 
የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ያላትን ራዕይ ለማሳካት የተጣለ ትልቅ መሰረት ነው።
 
ወጣቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሚጨብጡት ዕውቀት የራሳቸውን የፈጠራ መንገድ ከመክፈቱም በላይ፣ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካና በአህጉሪቱ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆና እንድትወጣ ያስችላታል።
 
በመሆኑም ይህን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ለሀገሪቱ ዘላቂ እድገትና ለወጣቱ ብሩህ ተስፋ ወሳኝ እርምጃ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም