ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያሳደገልን ነው

ጊምቢ፣ ነሐሴ4/2018 (ኢዜአ) ፡-በምዕራብ ወለጋ ዞን እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር  የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዳስገኘላቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

የ‘ሌማት ትሩፋት’ መርሃ-ግብር በኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለ ሀገራዊ የልማት ንቅናቄ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም በግብርናው ዘርፍ በዶሮ፣ በወተት፣ በማር፣ በበግና ፍየል ማድለብ እንዲሁም በዓሳ እርባታ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው። 

መርሃ-ግብሩ በቤተሰብ ደረጃ የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ፣ የገበያ አቅርቦትን በማሻሻል እና ለዜጎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ረገድም ትልቅ ድርሻ አለው።

በዚሁ መሠረት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን የመርሃ-ግብሩን አፈጻጸም ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል። 

በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች በዘመናዊ መንገድ የዶሮ እርባታ፣ የወተት ላሞች እንክብካቤ እና የማር ንብ እርባታ ላይ በስፋት እንዲሰማሩ መደረጉ ተገልጿል። 

ይህ እንቅስቃሴም በየቤተሰቡ ደረጃ ንጹህ እና የተመጣጠነ ምግብ በቀላሉ እንዲገኝ አስችሏል፤ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ከዘርፉ የሚያገኙትን ትርፍ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩና የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉም አድርጓል።

በዞኑ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመሳተፍ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የኢናንጎ ከተማ ነዋሪ አቶ ሂካ ኩመራ እና አለምነሽ አብዲ እንዳሉት አምስት የወተት ላሞች በማርባት በቀን በአማካይ 150 ሊትር ወተት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በተፈጠረላቸው ድጋፍና ዕድል በወተት ላም እርባታ ዘርፍ መሰማራታቸው፣ የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻልና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

ወይዘሮ ዲርቤ ሌሊሳ በበኩላቸው 300 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት በሥራቸው ትርፋማ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ለአካባቢው ማህበረሰብ እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውንና የራሳቸውን ገቢ ማሳደጋቸውን ገልጸው፤ በተጨማሪም ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ወጣት ሙቤ ቃሲም በበኩሉ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን በ500 ዶሮዎች የጀመረው የእርባታ ሥራ አሁን ላይ ውጤታማ እያደረገው መሆኑን ገልጸዋል።

የእንቁላል እና የሥጋ ዶሮዎችን ለገበያ በማቅረብ በሥራው ትርፋማ እየሆነ መምጣቱንም ተናግሯል።


 

የምዕራብ ወለጋ ዞን የኢናንጎ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል በዳሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች የመመለስ ሥራዎችን ከመስራት ጎን ለጎን የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይም በ‘ሌማት ትሩፋት’ መርሃ-ግብር ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞች፣ ዶሮዎች እና የንብ ቀፎዎች ለአካባቢው ነዋሪዎች እየቀረቡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ልማት እና ዝርያ ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ገመቺስ ታደሰ፤ በ‘ሌማት ትሩፋት’ መርሃ-ግብር በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ያስቻሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።


 

በተለይም ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞች አቅርቦትና በዶሮ እርባታ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ‘ሌማት ትሩፋት’ መርሃግብር 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩቶች ለአርሶ አደሮችና ወጣቶች የተሰራጩ ሲሆን፤ 5 ሺህ ላሞችን በማዳቀልም 90 ሚሊዮን 58 ሺህ ሊትር የወተት ምርት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዞኑ በ‘ሌማት ትሩፋት’ መርሃ-ግብር አማካኝነት የዓሳ እርባታ መንደሮች በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም