የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ ዕድልን ፈጥሮልናል - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ ዕድልን ፈጥሮልናል
ሀዋሳ ፤ነሀሴ 4/2018 (ኢዜአ)፡-የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዕድል እንደፈጠረላቸው የሀዋሳ ከተማ በጎ ፈቃደኞች ገለጹ።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በጤናና ትምህርትን ጨምሮ በ14 ዘርፎች የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ አስታውቋል።
በከተማዋ ደም በመለገስ የተሳተፉ በጎ ፈቃደኞች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜግነት ግዴታችንን እንድንወጣ ዕድልን ፈጥሮልናል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተሻለ ኤልያስ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተደጋጋሚ ደም በመለገስ ለወገናቸው በመድረስ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከወሊድ ጋር በተያያዘ እናቶች በሚያጋጥማቸው የደም መፍሰስ ምክንያት ሕይወታቸው እንዳያልፍ እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ መምህርት አይናለም አስፋው በበኩሏ፣ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በምታስተምርበት ትምህርት ቤት የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት በበጎ ፈቃደኝነት እየሠራች መሆኑን ገልጻለች።
በተጨማሪም ደም በመለገስ ለወገን ደራሽነቷን እያሳየች መሆኑን ጠቅሳ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ ላይ እየተሳተፈች እንደሆነም አክላለች።
ከጓደኞቿ ጋር በመሆን አቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸው ወገኖችን በመንከባከብና ቤት በመጠገን ተሳትፎ እያደረገች እንደምትገኝ የገለጸችው ደግሞ ወጣት ንግሥት ጸጋ ናት።
በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ወልደጻድቅ፣ በከተማው በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ14 ዘርፎች ከ90 ሺህ በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ወጣቶቹ በደም ልገሳ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ ቤት በማደስና በመጠገን፣ በማዕድ ማጋራት፣ በከተማ ጽዳትና ውበት እንዲሁም በሌሎች ተግባራት የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 90 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን በመሥራት፣ ከ246 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥትን ወጪ ለማዳን የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ኃላፊዋ አስረድተዋል።