በአማራ ክልል ከዘንድሮ ዓመት የበልግ ሰብል ልማት ከሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከዘንድሮ ዓመት የበልግ ሰብል ልማት ከሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በበልግ ወቅት ከለማው ሰብል ከሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በመኸር፣ በመስኖና በበልግ ልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተቻለ ነው።
በበጋው ወቅትም የበልግ አብቃይ በሆኑ ዞኖች 247 ሺህ 367 ሄክታር መሬት በማልማት ከሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የተገኘው ምርትም የገብስ፣ ስንዴ፣ አኩሪ አተር፣ ቦሎቄ፣ ጤፍ፣ ማሾና ሌሎች ሰብሎች መሆኑን ጠቁመው፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የሁለት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው ብለዋል።
ይህም አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እያረጋገጠ እንዲመጣ ከማድረግ ባለፈ፤ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለወጭ ንግድ የሚሆን ምርት በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የተሁለደሬ ወረዳ አርሶ አደር ኢብራሂም አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ በዘንድሮው የበልግ ዝናብ አንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸውን ቦሎቄና ሽምብራ በመዝራት የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ይህም በምግብ ራሴን እንድችል ከማድረግ ባለፈ ከምግብ ፍጆታ የተረፈውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንድሆን አስችሎኛል ብለዋል።
የበልግ ዝናብ ስርጭቱ የተሻለ በመሆኑ በግማሽ ሄክታር መሬት ካለሙት የገብስ ሰብል 15 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን የጣርማ በር ወረዳ አርሶ አደር አሰፋ መኮነን ናቸው።
በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ በበልግ ሰብል ከለማው ከ146 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።