ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ታርሶ በዘር ተሸፍኗል

አዳማ፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፡-በአዳማ ከተማ ከልማት ሥራዎች ጎን ለጎን ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን የከተማዋ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

አዳማ ከኦሮሚያ ክልል ዋነኛ የኢኮኖሚ፣ የኢንዱስትሪ እና የትራንስፖርት ማዕከላት መካከል አንዷ በመሆኗ ፈጣን የከተማ ማስፋፋትና የህዝብ ቁጥር እድገት የሚታይባት ከተማ ናት። 

የከተማዋ የቆዳ ስፋትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በየጊዜው እያደገ ቢመጣም፣ ከተማን ከአካባቢ ጥበቃ እና ከምግብ ዋስትና ጋር አጣጥሞ ማስኬድ አስፈላጊ ነው።

ይህ እርምጃ የከተሞች ህዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የሚከሰተውን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት እና አትክልትና ሰብል ምርቶች አቅርቦትን ጨምሮ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ፣ እንዲሁም ለወጣቶች እና ለሴቶች በከተማ ግብርና እና በዘመናዊ የእርሻ ስራዎች የስራ እድል ለመፍጠር  ታስቦ የሚተገበር ይሆናል።

የአዳማ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤት እንደገለፀው ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑ፣ ከተማዋ የማኑፋክቸሪንግ እና የንግድ ማዕከልነቷን እንደጠበቀች የግብርና ምርታማነቷንም ጎን ለጎን ለማሳደግ እያደረገች ያለውን ጥረት የሚያሳይ ነው።


 

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አለሙ ቂልጡ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2018/19 የምርት ዘመን የከተማዋን አርሶ አደር ምርትና ምርታማነት ለመጨመር በተሻለ ደረጃ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ቀርቧል።

ከምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳና ሉሜ ወረዳ 28 የገጠር ቀበሌዎችን በማጠቃለል እንደገና የተደራጀችው አዳማ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ወደ ከተማዋ መቀላቀላቸውንም ሃላፊው ገልጸዋል።

በዚህም ከተማዋ የነበራት የእርሻ መሬት ከእጥፍ በላይ ማደጉን የገለጹት አቶ አለሙ፤  የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የእርሻ አሰራር ስርዓቱ በቴክኖሎጂና በሜካናይዜሽን የታገዘ እንዲሆን በተደረገው ጥረት   ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።


 

ለዘንድሮ የመኽር እርሻ ልማት በአስተዳደሩ 20 የእርሻ ትራክተሮች ተገዝተው ለአርሶ አደሩ መሰጠቱን ገልጸው፤ እስካሁን 25ሺህ 154 ሄክታር መሬት በስንዴ፣ ጤፍ፣ ቦቆሎና ጥራጥሬን ጨምሮ በዋና ዋና ሰብሎች ተሸፍኗል ብለዋል።

በመኽር እርሻው ከ50ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ፀረ አረም መድሃኒቶች ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱንም አቶ አለሙ ጨምረው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የከተማዋን አርሶ አደር ህይወት ከመሰረቱ ለመለወጥ ከዋና ዋና የሰብል ልማት ባለፈ ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት የሚችሉና ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን መተካት በሚችሉት የፍራፍሬ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። 

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ላይ አቮካዶ፣ ብርትኳን፣ ሎሚ፣ ፓፓየ፣ ዘይቱንና ማንጎ በስፋት እየለማ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም የአዋሽ ወንዝን ጨምሮ የመስኖ ውሃ ተቋማትን በመጠገንና የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ በዓመት ከሶስት ጊዜ በላይ የማምረት ሂደት ባህል እንዲሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም