ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው ሂደት ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሂደት ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡

የምክክሩ አካሄድ የውሳኔ የመስጠት ሂደት ሳይሆን ምክረ ሀሳብ ማቅረብ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክር ሂደቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፣ የምክክር ሂደቱ እየተጠናከረና ወደ ተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ከ10 እና ከ50 ተሳታፊዎች ተነስተው የነበሩ ሀሳቦች ወደ 250 ቡድኖች ማደጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ባለው ደረጃ ሁለቱ የ250 ቡድኖች የተነጋገሩባቸውንና የሰሯቸውን ስራዎች አጠናቅረውና ሰንደው ለ500ዎቹ ቡድኖች ማቅረብ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የቀጣዩን ምዕራፍ የጀመሩ የ500 ቡድን አባላት የቀረቡላቸውን ሀሳቦች በማዳመጥ፣መካተት ያለባቸውንና የሚገባቸውን ሀሳቦች በደንብ እያዳበሩ ይገኛሉ ብለዋል።

እስካሁን 250 ሆነው በመወያየት ላይ የሚገኙ ተመካካሪዎች ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሚጨርሱ እና ነገ ጠዋትም የሚጨርሱት ደግሞ ነገ ከሰአት በኋላ ለ500 ቡድኖቻቸው የሚያቀርቡ ይሆናል ብለዋል።

በሂደቱ መጀመሪያ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች፣ ክርክሮች እና የተለያዩ ስሜት መንጸባረቆች መታየታቸው የምክክሩን አሳታፊነት እና ህያውነት የሚያሳዩ ተፈጥሮአዊ የውይይት ማሳያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የተለያዩ ሀሳብ የመስጠት ፍላጎቱ የሚመጣው ተሳታፊዎች የየራሳቸውንና የረጅም ጊዜ ጥያቄዎቻቸውን ለማንጸባረቅ ትክክለኛው አጋጣሚ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው ብለዋል።

አልፎ አልፎ የሚታዩ ስሜታዊነት በምክክር ኮሚሽኑ የስብሰባ ስነ-ስርዓት ደንብ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

በምክክር ሂደቱ ውስጥ አንደኛው መርህ መከባበር ሲሆን፣ ሁለተኛው መነጋገር፣ መደማመጥና ወደ መሀል መምጣት በመሆኑን ተመካካሪዎች ይህንን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።

ተሳታፊዎች የመጡት በየመንደሩና በየአካባቢው ያለውን ጥያቄ እዚያው እንዲመለስ ለማድረግ ሳይሆን ኢትዮጵያን ማዕከል አድርገው መመካከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የምክክሩ አካሄድ የውሳኔ የመስጠት ሂደት ሳይሆን ምክር ሀሳብ ማቅረብ መሆኑን ጠቁመው፤ ምክረ ሀሳቦቹ ለህግ አስፈጻሚው፣ ለህግ አስከባሪው፣ ለህግ አውጪው፣ ለህግ ተርጓሚው፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሲቪል ማህበራት የሚተላለፉ ናቸው ብለዋል።

"በድምፅ ብልጫ ውሳኔ ይሰጣል" ወይም "ከውስጥና ከውጭ ጫና ተደርጎ ውሳኔ ሊያስተላልፉ ነው" የሚባለው ወሬ ከአሉባልታ ያለፈ አይደለም ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በተመካካሪዎች መካካል የሚታዩ ክርክሮችና አለመግባባት በ"ዳይቨርጀንስ" (የመበታተን) ምዕራፍ ላይ ያለ በመሆኑ አግባብነት ያለውና ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ መሰብሰብ ምዕራፍ (ኮንቨርጀንስ) ስንመጣ የራሳችንን የግል ሀሳብ እየጣልን ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ የጋራ ሀሳብ ይዘን እንሄዳለን ብለዋል።

በጣም ያጨቃጭቃሉ ተብለው የነበሩ አጀንዳዎች ቀደም ብለው ህዝቡ "የጋራችን ነው" በማለት ወደ መሀል ያመጣቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ምክክሩ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ከአንድ ወር ልፋት በኋላ በሚቀጥሉት አንድ እና ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከ4ሺህ ተሳታፊዎች ጋር ያለው የምክክር ሂደት ይገባደዳል ብለዋል፡፡

ከዚያ በኋላ ኮሚሽኑ የመጡት ሀሳቦች አጠናክሮ ለተግባራዊው አካል የሚላኩ ሲሆን፣ መተግበራቸውም እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሆነው ሂደቱን በትህትና ለሚከታተሉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም