ቀጥታ፡

​​​​​​​በምክክር ጉባኤው የሚተላለፍ ውሳኔ የለም - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሚተላለፍ ውሳኔ እንደሌለና ዋና ዓላማው ለተግባራዊ አካላት ምክረ ሀሳቦችን ማዘጋጀት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ከ10ሩ ቡድኖች የተውጣጡ ሁለቱ የ250 አባላት ስብስብ ያዘጋጁትን ሃሳብ በጋራ እያጠናቀሩ እንደሚገኝ ዋና ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።

በመቀጠልም እነዚህ ሁለቱ የ250 ቡድኖች በጋራ በመሆን ለ500 አባላት የተወያዩባቸውን ሀሳቦች ለ500ዎቹ እያቀረቡ እንደሚገኝና ይህ ሂደት ቀጣይነት እንዳለው ጠቁመዋል።

ባለ 500ዎቹ የአጀንዳ ቡድኖች በሃሳቦቹ ላይ አስተያያት በመስጠት አጀንዳዎቹ እንዲዳብሩ እያደረጉ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በአሁኑ ሰዓት የ500 ምክክር መጀመሩንና ሁሉም የ500 ተመካካሪ ቡድኖች በሁለት ቀናት ሙሉ ለሙሉ ወደ ምክክር እንደሚገቡም ጠቁመዋል።

ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተመካካሪዎች የተለያዩ ሀሳቦችና ጥያቄዎችን በማንሳት እየመከሩ እንደሚገኝና አጠቃላይ ሂደቱ ጥሩ የሚባል እንደሆነ አንስተዋል።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚወሰን ውሳኔ የለም ያሉት ዋና ኮሚሽኑ የሂደቱ ዋና አላማ ምክረ ሀሳቦችን ማቅረብ ነው ብለዋል።

በጉባኤው የሚቀርቡ ምክር ሀሳቦች መንግስት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጨምሮ በተግባሪ አካላት እንደሚፈጸሙ አስገንዝበዋል።

በምክክሩ ላይ እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች ሊተላለፉ ነው የሚሉ ሀሳቦች ከአሉባልታ የዘለለ ትርጉም እንደሌላቸው ተናግረዋል።

የምክክር ጉባኤው አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ የተለያዩ የማይስማሙ ሀሳቦች መነሳታቸው አግባብና ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑን ጠቅሰው ይህም በቀጣይ ሀሳብን ወደ መሐል ለማምጣት ሂደት ወሳኝ መሰረት እንደሚጥል ነው ያነሱት።

የመሰባሰብ ምዕራፍ ላይ ሲደርስ የግል ሀሳቦች እየተጣሉ ኢትዮጵያን ያማካሉ የጋራ ሀሳቦች እንደሚመጡም አንስተዋል።

በስምንቱ አጀንዳዎች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች በቀጣይ የተሻለ ምክረ ሀሳቦች እንደሚገኝባቸው ዋና ኮሚሽነሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም