የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከላ፣ክትትልና የፅድቀት መጠን በጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ እየተረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከላ፣ክትትልና የፅድቀት መጠን በጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ እየተረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተከላ፣ ክትትልና የፅድቀት መጠን በጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ እየተረጋገጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢንስቲትዩቱ የካርታ ስራ መሪ ስራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሳይንሳዊ የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ፣በጂፒኤስ (GPS) ልኬትና በሳተላይት ምስል ትንተና መደገፍ መጀመሩ በመረጃዎች ጥራትና በውጤታማነት በኩል ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል።
የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ በዋናነት የመረጃዎችን የት፣እንዴት እና መቼ የሚሉ ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች በትክክል መመለስ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ፣በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ የሚተከልባቸው ቦታዎች በጂፒኤስ ንባብ አማካኝነት መጋጠሚያቸው ተለይቶ የተመዘገቡና ያልተመዘገቡ ተብለው ይከፈላሉ።
በቅርቡ በተካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ብቻ ከ291 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሙሉ በሙሉ በጂፒኤስ ተለክቶና የቦታ ስፋቱ ተሰልቶ መደራጀቱን ጠቁመዋል።
ይህ አሰራር ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የመረጃ መደጋገሞችንና የመረጃዎች መሳሳትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረቱን ገልፀዋል።
አሁን ተግባራዊ በተደረገው አሰራር መረጃው ቢሮ እንደደረሰ በሳተላይት ምስል እንደሚረጋገጥ ጠቁመው፤ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ባለሙያዎች በአካል በመገኘት የማረጋገጥ ስራ እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል።
ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አለመሆኑን በመግለጽ፣የተተከሉ ችግኞች ማደጋቸውንና የአካባቢውን አረንጓዴነት መለወጣቸውን ለመከታተል የርቀት ቴክኖሎጂ (Remote Sensing) ትንተና ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ባለሙያዎች የደረቅ ወቅት የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም የመሬት ሽፋኑን (የከተማ፣ የእርሻ፣ የወንዝ እና የደን) የሪፍሌክታንስ (Reflectance) ዋጋ በመተንተን ትክክለኛውን የደን ሽፋን እንዲለዩ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህ ሳይንሳዊ መንገድ በተካሄደው ዳሰሳና በመስክ ማረጋገጫ ስራ፣ ቀደም ሲል 17 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በአሁኑ ወቅት ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉ መረጋገጡን ገልጸዋል።
ይህ ትልቅ ስኬት የተገኘው ህብረተሰቡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ባደረገው ያልተቋረጠ ጥረትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተከናወኑ ስራዎች መሆኑንም አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጃቸውን የደን፣ የሰብልና የከተማ መረጃ ክትትልን ጨምሮ 10 ማዕከላትን በመጠቀም መረጃዎችን ለውሳኔ ሰጪዎችና ለግብርና ሚኒስቴር ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።