ቀጥታ፡

ወጣቶች ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እኩል መራመድ አለባቸው- የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ቤተልሔም ደሴ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦ ወጣቶች ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እኩል በመራመድ ራሳቸውን በክህሎት ብቁ እንዲያደርግ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ቤተልሔም ደሴ ጥሪ አቀረበች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረበውን የኢትዮጵያ ወጣቶች የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭን እንዲቀላቀሉ እና የክረምቱ ወቅት ከመጠናቀቁ በፊት የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ 7 ሚሊዮን ለማድረስ የተደረገውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተናጋጅነት በኢኒሼቲቩ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

‎በመቀጠል በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ልምዳቸውንና እይታቸውን ያካፈሉ አራት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብር ላይ ታሪኳን ያካፈለችው የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ቤተልሔም ደሴ፤ የቴክኖሎጂ ሕይወቷ ከአስራ ሰባት ዓመት በፊት ገና የአስር ዓመት ታዳጊ ባለችበት ወቅት እና የዲጂታል አማራጮች ጨርሶ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ እንደተጀመረ ገልጻለች።

ያለፈውን ጊዜ ከአሁኑ ጋር በማነጻጸርም፣ ዛሬ ላይ ቴክኖሎጂ በስፋት ተደራሽ በመሆኑ የአሁኑ ዘመን ወጣቶች ህልማቸውን ለማሳካት የሚያስችል ምቹ መንገድ እንዳላቸው አመላክታለች።

ይህ ትልቅ ዕድል ቢኖርም ስኬት ግን ፈጣን እርምጃን እንደሚጠይቅ ያስገነዘበችው ቤተልሔም፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመጠባበቅ ወጥተው አሁኑኑ የለውጥ መሪ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እኩል ለመራመድ ራሳቸውን በክህሎት በንቃት እንዲያበቁ ጥሪዋን አስተላልፋለች።

‎ለተጨማሪ መረጃ እና ለመመዝገብ፦ ethiocoders.et

#PMOEthiopia #DigitalEthiopia2030 #5MillionEthiopianCoders

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም