ወጣቶች ክህሎታቸውን በማሳደግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው- አብዮት ባዩ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ክህሎታቸውን በማሳደግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው- አብዮት ባዩ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4 /2018(ኢዜአ)፦ ወጣቶች ክህሎታቸውን በማሳደግ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስኬት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረበውን የኢትዮጵያ ወጣቶች የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭን እንዲቀላቀሉ እና የክረምቱ ወቅት ከመጠናቀቁ በፊት የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ 7 ሚሊዮን ለማድረስ የተደረገውን ሀገራዊ ጥሪ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተናጋጅነት በኢኒሼቲቩ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመቀጠል በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ልምዳቸውንና እይታቸውን ያካፈሉ አራት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) በፓናል ውይይቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፦ የላቁ የዲጂታል መድረኮችን መገንባት እና ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል አሰራር መሸጋገር ግድ መሆኑን ገልጸው ለተግባራዊነቱና የዘመነ አፈጻጸም የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የሰዎችን አቅም ማጎልበት፣ አሳታፊ የዲጂታል ምህዳር መፍጠር፣ ተዳራሽነትን ማስፋፋት እና ሀገሪቱን የዲጂታል ማዕከል ማድረግ ላይ ትኩረት ባደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግቦች ስር እያንዳንዱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚመዘገብ ስኬት ሙሉ በሙሉ በሰው ሃይል አቅም ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አብራርተዋል።
ይህን አቅም ወደ ተግባር ለመቀየር ደግሞ ወጣቶች በየተሰማሩበት ዘርፍ ክህሎታቸውን በንቃት ማሳደግ እና ለላቀ ውጤታማነት መጠንከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።