ቀጥታ፡

ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝብን የልማት ጥያቄ የመመለስ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና፤  ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝብን የልማት ጥያቄ የመመለስ ተግባራት እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (/) ገለፁ።

የክልሉ ገቢዎች እና ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች በሕገ-ወጥ የንግድ ቁጥጥር፣ ኑሮን ማረጋጋትና የታክስ ሕግ ተገዢነትን በማረጋገጥ ዙሪያ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች የመመለስ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የገቢ አቅምን በማሳደግ የከተሞችን ገጽታ የመቀየር፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን የማስፋትና የማህበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት የተመዘገቡ ስኬቶች ይጠናከራሉ ብለዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን የተሳለጠ አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም ሕገ-ወጥነትን የመከላከል፣ የግብይት ማዕከላትን የማስፋፋት፣ ምርትን በበቂ ሁኔታ የማቅረብ፣ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠርና የሸማች ማኅበራትን የማጠናከር ሥራዎች እንደሚከናወኑ አክለዋል፡፡


 

በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማሳለጥና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ወሳኝ በመሆናቸው፣ መስተዳድሩ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ ሥራ ማጠናከር የትኩረት አቅጣጫው ማድረጉንም ገልጸዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የመንግሥትና የፓርቲ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም