በደቡብ ወሎ ዞን እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ለእንቅስቃሴና ለልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ለእንቅስቃሴና ለልማት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
ደሴ ፤ ነሐሴ 4/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ወሎ ዞን እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር እንዲነቃቁ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የዞኑ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የመሰረተ ልማት ቡድን የኮንስትራክሽን አስተዳደር መሃንዲስ አደም መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሐይቅ፣ ጊምባ፣ መካነሰላም፣ ሀርቡ፣ ወረኢሉ፣ አቀስታ እና ደጎሎ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተካሔደ ነው።
በነዚሁ አካባቢዎች በመገንባት ላይ ካለው 6 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ውስጥም ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከተሞችን በማስዋብና ገጽታቸውን በመቀየር እንዲነቃቁ ከማድረጉ ባለፈ ለነዋሪዎች፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ቀሪውን ሥራ በፍጥነትና በጥራት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አክለዋል።
ልማቱ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ መዝናኛዎችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያካተተ በመሆኑ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉን ነው የጠቀሱት።
ማሕበረሰቡ ለግንባታ ስራው በገንዘብ፣ በጉልበትና ቁሳቁስ በማቅረብ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የሐይቅ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እናትነሽ በሽር በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ከተማዋን ከማነቃቃቱ በላይ ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተለይም የእግረኛ፣ የተሽከርካሪና የብስክሌት መንገዶችን እንዲሁም መዝናኛዎችን ማካተቱ የትራፊክ አደጋን በማስቀረት በነጻነት ለመንቀሳቀስ አስችሎናል ነው የሚሉት።
ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ ሸህ ጀማል ለይሱ፤ ልማቱ የከተማዋን ገጽታ በማሳመርና በማስዋብ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ነው ያብራሩት።
ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጉልበት ያደረገው አስተዋጽኦ የግንባታ ስራው በፍጥነትና በጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ማድረጉን ገልፀዋል።