በጋምቤላ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት ከ86 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት ከ86 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ለምቷል
ጋምቤላ፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በተያዘው የመኸር ወቅት ከ86 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሰሊጥ ልማት መከናወኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።
የጋምቤላ ክልል ሰፊና ለም መሬት፣ በቂ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ ሀብት እንዲሁም ለተለያዩ የግብርና ምርቶች ተስማሚ የሆነ አየር ንብረት ያለው አካባቢ ነው።
ክልሉ በተለይም ለቅባት ሰብሎች አመቺ በመሆኑ በሀገሪቱ የግብርና ኢንቨስትመንት ከተመረጡ ዋና ዋና አካባቢዎች አንዱ ያደርገዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ የሚካሄደው የቅባት ሰብሎች ልማት በዋናነት በባህላዊ መንገድ በአርሶ አደሮችና በጥቂት ባለሃብቶች የተወሰነ የነበረ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዘመናዊ የግብርና ግብአቶች እና በሜካናይዜሽን ታግዞ በፍጥነት እያደገ ይገኛል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጀሉ ኡሞድ ለኢዜአ እንደገለጹት ክልሉ የቅባት ሰብሎችን ጨምሮ ለሁሉም የግብርና ልማት ምቹ ስነ- ምህዳር ያለው አካባቢ ነው።
ክልሉ ለሁሉም የግብርና ልማት የተመቸ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የቅባት እህሎችን ጨምሮ በሌሎች ሰፋፊ የግብርና ልማት ለመሰማራት በርካታ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ እየገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የመኸር እርሻ በባለሃበቶችና በአርሶ አደሮች ከ86 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ መልማቱን ገልጸዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የመኸር ወቅት የለማው መሬት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ ከለማው ሰሊጥም ከ516 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ሊሰበሰብ እንደሚችል ጠቁመው፤ አሁን ላይ ያለው የሰብሉ ቁመና የተሻለ ስለሆነ ከተጠበቀው በላይ ምርት ሊገኝ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በክልሉ አቦቦ ወረዳ በሰሊጥ ሰብል ልማት ከተሰማሩት ባለሃብቶች መካከል አቶ እየሩስ ዓለሙ በሰጡት አስተያየት የዘንድሮው ክረምት የዝናብ ስርጭት ቀለል ያለ በመሆኑ ለሰሊጥ ሰብል ምቹ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በ120 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት ሰብል ደርሶ በመሰብሰብ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው የዘንድሮው የሰሊጥ ምርት በብዛትም ሆነ በጥራት የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።