የሃሳብ ብዘኃነት ለሀገራዊ ምክክር ግብዓት ወይስ ፈተና? - ኢዜአ አማርኛ
የሃሳብ ብዘኃነት ለሀገራዊ ምክክር ግብዓት ወይስ ፈተና?
ሀገራዊ ምክክር ያስፈለገው የአንድ ሀገር ዜጎች መሰረታዊ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ስላላቸው አይደለም። ይልቁንም አብረው እንዲመክሩ የሚያደርጋቸው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተለያየ ሃሳብ (አመለካከት) በማራመዳቸው ነው። ስለዚህ ሂደቱ የተለያየ ልምድ፣ ዕይታ እና ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ስለ ጋራና የወደፊት ሀገራቸው የሚያስቡበትን ዕድል ይፈጥራል።
በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሁሉም ተመካካሪ የራሱ ታሪክ አለው፡፡ በሂደቱ አንዱ ሌላውን ለማድመጥ ብሎም ለማወቅ ካልሞከረ ከሃሳቡ ጀርባ ያሉ ፍላጎቶችን ሊያውቅ አይችልም፤ ያም እርስ በእርስ ለመተዋወቅ እና ለመግባባት የሚደረገውን ጥረት ምሉዕ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡
የልዩነት ጥንካሬ የሚገኘውም እዚህ ላይ ነው። በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የሃሳብ ብዘኃነት መኖሩ እያንዳንዱን ሃሳብ እንድንፈትሽ መንገድ ይጠርጋል። ሌሎችን ለማዳመጥ፣ ጥያቄ ለመጠየቅ እና የማናውቀውን ለመረዳት ዕድል ይሰጠናል። ይህም የጋራ ግንዛቤን በማሳደግ የተሻሉ የጋራ ውሳኔዎችን ለመወሰን በር ይከፍታል፡፡
ነገር ግን የሃሳብ ልዩነት መኖር ብቻውን ለሀገራዊ ምክክር መጎልበት በቂ አይሆንም። የሃሳብ ልዮነቶች ትርጉም ያለው ጥቅም ሊያመጡ የሚችሉት ተመካካሪዎች የሃሳብ ልዮነቶቻቸውን በመከባባር ማስተናገድ ሲችሉ እና እርስ በእርስ ሲደማመጡ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ልብ እንበል! የሀገራዊ ምክክር ዓላማ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ሃሳብ እንዲያራምድ ማድረግ አይደለም። ሂደቱ ልዩነቶችን ወደ መማማር፣ መግባባት እና ችግር መፍቻ አቅም በመቀየር የጋራ የሆነ የመግባባትን መንገድ የምንቀይስበት መሆኑን ማስተዋል ይገባል።
ስለዚህ ሀገራዊ ምክክር “ልዩነቶቻችንን በበቂ ሁኔታ ተረድተን እንዴት የጋራ መንገድ እንፍጠር?” ብሎ ይጠይቃል።
የተለያዩ ዕይታዎች በአክብሮት ሲደመጡና በጥሞና ሲታዩ፣ ሀገራዊ ምክክር ወደ ተሻለ የመግባባት መንገድ፣ ሰፋ ያሉ መፍትሔዎች ወደ ማምጣት እና ወደ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት ሊያመራ ይችላል።
እናስታውስ! የሃሳብ ልዩነት የሀገራዊ ምክክር መለያ ቀለም ነው። ነገር ግን በምክክር ሂደት ውስጥ ልዮነቶችን የምናስተናግድበት መንገድ የሰለጠና እና ሰብዓዊነት የተሞላው ሊሆን እንደሚገባ መዘንጋት የለብንም!
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!
ነሀሴ 4/2018 ዓ.ም