ቀጥታ፡

የአፍሪካ የውሃ ማማ ኢትዮጵያ ሳትሆን ግብፅ ናት!

  • ግብጽ ራሷን የምትስልበት የውሃ እጥረት ትረካ ከነባራዊ ሁኔታም በእጅጉ የተቃረነ ነው።

የአፍሪካን የታሪክ፣ የኢኮኖሚና ጂኦ-ፖለቲካ  በከፍተኛ ሁኔታ ከሚቃኙት ተፈጥሯዊ ሃብቶች መካከል ውሃ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።

አፍሪካውያን የውሃ ሀብታቸውን በጋራ አልምቶ የመጠቀም ፍላጎታቸውና ጥረታቸው የአህጉሪቱን የወደፊት የልማትና የሰላም አቅጣጫ የሚወስን ወሳኝ ጉዳይ  ቢሆንም ይህ አህጉራዊ የትብብርና የጋራ እድገት መንፈስ እውን ሊሆን የሚችለው የተፋሰሱ ሀገራት ያላቸውን እውነተኛ የውሃ ሀብት መጠንና ፍላጎት በሳይንሳዊ እውነታዎችና በግልጽኝነት ላይ መስረተው ሲተገብሩት ብቻ ነው።

በዚህ አህጉራዊ የተፋሰስ ትብብር ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዘው የታላቁ ዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ነው። ሆኖም ለዘመናት የዘለቀውና አሁንም ድረስ በዲፕሎማሲው መድረክ የሚንጸባረቀው ዋነኛው ማነቆ ግብፅ እራሷን "ለከፍተኛ የውሃ እጥረት የተጋለጠችና ፍጹም የዓባይ ጥገኛ የሆነች ብቸኛ ሀገር" አድርጋ የምታቀርብበት ትርክት ነው። ይህ ትረካ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብን ሲያደናግር ቆይቷል።

ነገር ግን የጂኦግራፊ፣ የሃይድሮሎጂና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ መረጃዎችን በጥልቀት ስንመረምር ግብፅ እራሷን የምትስልበት የውሃ እጥረት ትረካ ከእውነተኛው  ነባራዊ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የሚቃረን ሆኖ እንገኘዋለን።

ግብፅ በውስጧ የያዘቻቸውን ግዙፍና ያልተነኩ ድብቅ ሀብቶች፣ የቴክኖሎጂ አቅሞችን እና በበረሃ ውስጥ የምታከናውናቸውን ሰፋፊ የውሃ ማዞር ፕሮጀክቶች ስንመለከት ሀገሪቱ እውነተኛ የውሃ እጥረት ሳይሆን ከፍተኛ የውሃ ሀብት ያላት መሆኗን በግልጽ ያሳያል።

ይህንን እውነታ በግልጽ የሚያስረዱትንና የግብፅን እውነተኛ የውሃ ማማነት የሚያረጋግጡትን ዋና ዋና ሳይንሳዊና ተግባራዊ ማስረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፦

የከርሰ ምድር ውሃ

ከገፀ-ምድር ውሃ ባሻገር በግብፅ፣ ሊቢያ፣ ሱዳን እና ቻድ ስር የሚገኘው የኑቢያ አሸዋማ ድንጋይ የከርሰ-ምድር ውሃ ስርዓት (Nubian Sandstone Aquifer System) በዓለም ላይ ካሉ የከርሰ-ምድር ውሃዎች ትልቁ ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በግብፅ ግዛት ስር ብቻ የሚገኘው የዚህ ውሃ መጠን 5 ትሪሊዮን እስከ 10 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሆነ ይገመታል። ይህ ግዙፍ ሀብት የዓባይ ወንዝን የአምስት ክፍለ-ዘመናት (500 ዓመታት) አጠቃላይ የውሃ ፍሰት የሚበልጥ ድብቅ ሃብት ነው። ግብፅ ይህንን ሀብቷን በዘመናዊ መንገድ አውጥታ ብትጠቀም ለበርካታ አስርት ዓመታት ያለ ምንም የገፀ-ምድር ውሃ ስጋት መኖር የሚያስችላት ስትራቴጂካዊ ክማቸት አላት ማለት ነው።

የአስዋን ከፍተኛ ግድብና የናስር ኃይቅ

የግብፅ የውሃ መከላከያ ማዕከል የሆነውና በአስዋን ከፍተኛ ግድብ የተገደበው ናስር ሀይቅ እስከ 169 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም አለው። ይህም ማለት በናስር ሃይቅ የተከማቸው ውሃ ብቻ የግብፅን የዓመታት ሙሉ የውሃ ፍላጎት ያለ ምንም ተጨማሪ የወንዝ ፍሰት መሸፈን የሚያስችል ግዙፍ ስትራቴጂካዊ መያዣ (Buffer) ሆኖ ያገለግላል።

የባሕር ውሃ ማጣራት አቅምና የግብጽ 2050 ማስተር ፕላን

ግብፅ በሜዲትራኒያን እና በቀይ ባህር ረጅም የባህር ዳርቻዎች ያሏት በመሆኑ በጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ትልቅ እርምጃ  እየወሰደች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት በቀን 1 ነጥብ 5 እስከ 2 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተጣራ ውሃ እያመረተች ሲሆን፤ በግልና በሕዝብ በካርቦን ቅነሳ ድጋፎች እና በባህር ዳርቻ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የማጣራት አቅሟን በጥሬው በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል እስከ 2050 የሚዘልቅ ስትራቴጂካዊ ማስተርፕላን አዘጋጅታለች።

ግዙፍ የውሃ ማዞር ፕሮጀክቶች

ግብጽ በቶሽካ ፕሮጀክት አማካኝነት ከናስር ሀይቅ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኩቢክ ሜትር ውሃዎችን ወደ ምዕራብ በረሃ በመቀየር ሰው ሰራሽ ሀይቆች እና ክፍት የመስኖ ቦዮች እንዲፈጠሩ  አድርጋለች ። በሌላ በኩል  ኒው ዴልታ እና ጂሪያን በሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት እና አዳዲስ ከተሞችን ለመገንባት የተፈጥሮ የአባይ ወንዝን አቅጣጫ በመቀየር ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ውሃ በመመደብ ላይ ትገኛለች።እነዚህ ፕሮጀክቶች ግብፅ ለትልልቅ የበረሃ ልማቶች የሚተርፍ ትርፍ ውሃ እንዳላት  በተግባር የሚያሳዩ ናቸው።

ውሃን መልሶ የመጠቀም አቅም

ግብፅ ውሃን  መልሶ በማጣራት ጥቅም ላይ ለማዋል ትልልቅ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎችን ለምሳሌ በህር ኤል ባቃር (Bahr El-Baqar plant) ገንብታለች። ሀገሪቱ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኩቢክ ሜትር ፍሳሽ ውሃዎችን መልሳ በመጠቀም ለግብርና በማዋል  የምትጠቀመውን እያንዳንዱን የውሃ ጠብታ የማባዛት ከፍተኛ ቴክኖሎጂያዊ አቅም እንዳላት አስመስክራለች።

መደምደሚያ

አፍሪካውያን የውሃ ሀብታቸውን በጋራ አልምተው ለመጠቀም የሚያደርጉት ጉዞ እውን ሊሆን የሚችለው ግብጽ የምታራምደውን አይነት  የተሳሳቱ ትርክቶችን  በሳይንሳዊ እውነታዎች መተካት ሲቻል ብቻ ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህን በሚገባ ሊገነዘብ ይገባል። ግብፅ ግዙፍ የከርሰ-ምድር ውሃ፣ ዘመናዊ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች፣ ከፍተኛ የውሃ መልሶ መጠቀም አቅም እና በበረሃ ውስጥ ውሃ እስከ ማዞር የሚያስችል ሀብት ያላት ሀገር ናት። ይህም ግብፅ የውሃ እጥረት ያለባት ሀገር ሳትሆን፣ የአፍሪካ የውሃ ማማ  መሆኗን በተግባር የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም