በአፋር ክልል የጠቅላይ ፍርድ ቤት አሰራሮችን በማቀላጠፍ የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የጠቅላይ ፍርድ ቤት አሰራሮችን በማቀላጠፍ የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ ተችሏል
ሰመራ፣ ነሀሴ 3/2018 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል የጠቅላይ ፍርድ ቤት አሰራሮችን በማቀላጠፍ የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ መቻሉን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ ገለጹ።
የአፋር ክልል ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ዘመን፣ 5ኛ የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን በማካሄድ ላይ ነው።
በዛሬ ሁለተኛ ቀን ውሎው የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሪፖርት ፕሬዚዳንቱ ሙሳ አብዶ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ዲጂታላይዜሽን አሰራርን በመተግበር የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ ተችሏል።
ይህም በፍርድ ቤቶች የነበረውን የሥራ ጫና ማስቀረቱን ተናግረው፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለአቤቱታ ከቀረቡ 14 ሺህ 309 መዝገቦች ውስጥ ከ13 ሺህ በላይ መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል ብለዋል።
በእዚህም አፈጻጸሙ 97 ከመቶ መሆኑን የገለፁት አቶ ሙሳ፣ ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የሦስት ከመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
ለውጤታማነቱም ተከታታይነት ያላቸው የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች ጥራትና ፍጥነት እንዲኖራቸው አሰራርን ከማዘመን ባለፈ የሰው ሀይሉን ለማብቃት መሰራቱንም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።