የክረምት ወቅት ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድሮች የወጣቶችን ስብእና የመገንባት ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የክረምት ወቅት ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድሮች የወጣቶችን ስብእና የመገንባት ሚና አላቸው
ደብረ ብርሃን፤ ነሐሴ 3/2018(ኢዜአ)፡-የክረምት ወቅት ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድሮች የወጣቶችን ስብእና ለመገንባት ሚና እንዳላቸው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድርን ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ አስጀምሯል።
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ከተማዋን የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማእከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለይም የስፖርት ዘርፉን በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራትና በሀገር እና ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩም ባለሀብቱንና ማህበረሰቡን በማስተባበር በየጊዜው የሚካሄዱ የታዳጊዎች ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድርን በልዩ ትኩረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
በክረምት ወቅት ወጣቶች ገዜያቸውን የሚያሳልፉበትን ስፖርታዊ ውድድር ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተጀመረው ውድድርም የዚህ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ተክለዮሐንስ ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው የክረምት ስፖርታዊ ስልጠናና ውድድሮች ታዳጊዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራ እንዳያሳልፉ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ዛሬ በተጀመረው የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ውድድር በ60 ቡድኖች የታቀፉ 1ሺህ 500 ስፖርተኞችን በማሳተፍ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
የውድድሩ ዓላማ ወጣቶች በስፖርታዊ ስነ ምግባር ከመታነጽ ባለፈ ተሰጧቸውን አውጥተው በማሳየት በቀጣይ ለትልልቅ ክለቦች የሚመረጡበትን እድል የሚከፍት ነው ብለዋል።
በተለይም ስፖርት ለሰላምና ለአንድነት ያለውን አበርክቶ በመጠቀም ወጣቶች አንድነታቸውን በማጠናከር ለአካባቢያቸው ሰላምና ልማት በጋራ እንዲሰለፉ ለማድረግ እንደሚካሄድ አስረድተዋል።
"የኮኮብ እግር ኳስ ቡድን" አሰልጣኝ ሐብታሙ መለሰ፣ የክረምት ውድድር መዘጋጀቱ ታዳጊዎች በስልጠና ያገኙትን የቴክኒክ እውቀት በተግባር የሚያሳዩበት ዕድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።
"የአንድነት እግር ኳስ ቡድን" አሰልጣኝ ታምራት ደስታ በበኩላቸው ውድድሩ የባህል ልውውጥ በማድረግ አንድነትንና መተሳሰብን ለማጎልበት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል
በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ የተጀመረው የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ለአንድ ወር የሚካሄድ መሆኑ ተመላክቷል።