ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት በመተግበር አልሚዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት በመተግበር አልሚዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ተችሏል
ጋምቤላ፤ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦ሀገሪቱ ያሏትን የኢንቨስትመንት እድሎች ለባለሀብቶች የማስተዋወቅ እና አገልግሎቶችን ቀልጣፋ የሚያደርጉ አሰራሮችን በመተግበር በርካታ አልሚዎችን ወደ ሀገር ውስጥ መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት አስፈፃሚ አካላት በጋምቤላ ከተማ እያካሄዱት ባለው የጋራ ምክክር በ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በአዲሱ በጀት ዓመት እቅድ በመምከር የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ አልሚዎችን ለመሳብ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ብቻ 528 የውጪ ሀገር ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
''ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ 2026 ፎረም’’ የኢንቨስትመንት ስምምነትንም የፈረሙ ሰባት ተቋማት 13 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ፈሰስ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የዲጂታል አገልግሎቱን በማስፋትና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከርና የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ተመራጭነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የኮሚሽኑ የስፔሻል ኢኮኖሚ ዞን ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዝናቡ ይርጋ በበኩላቸው፥ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ወደ ውጤት በመቀየር የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራሩ ይጠናከራል ብለዋል።
ለዚህም የመሰረተ ልማት አውታሮችን ተደራሽነት የማስፋትና የአሰራር ማእቀፎችን ማስፋት ላይ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ ባለሃብቶች ለሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቅንጅታዊ አሰራሮችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ በ2018 እቅድ አፈፃፀምና በአዲሱ በጀት ዓመት ውይይት በማድረግ የትኩረት አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ተሳፊዎች በዛሬው ዕለት ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሰተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ጋር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
በቀጣይም የልማት ምልከታ የመስክ ጉብኝት በማካሄድ መርሃ ግብራቸውን እንደሚያጠናቅቁ ይጠበቃል።