ለብዙዎች ብርሃን የፈነጠቀው የገጠር ሞዴል መንደር! - ኢዜአ አማርኛ
ለብዙዎች ብርሃን የፈነጠቀው የገጠር ሞዴል መንደር!
ለብዙዎች ብርሃን የፈነጠቀው የገጠር ሞዴል መንደር!
በቀደሰ ተክሌ (ከሚዛን አማን )
የገጠሩ ማህበረሰብ የጨለማ ኑሮ የተፈረደበት ይመስል ኑሮውን ማሻሻል ሳይችል እልፍ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ለዘመናት መብራትና ውኃ ለማግኘትና ከቴክኖሎጂ ጋር ተቀራርቦ ለመኖር ወደ ከተማ መሰደድ ብቸኛው አማራጭም ነበር።
የከተሜው ዋልታ የሀገር ኢኮኖሚ መሠረት የሚወሰንበት የአራሹ ገበሬ የኑሮ ደረጃ ባህላዊውን የአኗኗር ዘዬ ባለመልቀቁ ደስተኛ ጊዜ የሚያሳልፍበት ሂደት አድካሚ እንደሚሆን ግልጽ ነው።
የገጠሬው የተበታተነ የአኗኗር ሥርዓትም ለገጠሬው አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፤ የእዚህን የህብረተሰብ ክፍል ምርቱን እንጂ ኑሮውን የጠየቀ አልነበረም ቢባል ግነት አይሆንም።
ቀደም ሲል በነበሩ መንግስታት ከተማን እንጂ ገጠርን ማዘመን የሚያስብ ስለመኖሩ ያጠራጥራል፤ ይህም በሀገሪቱ ለኢፍትሐዊ ዕድገት የራሱን ተጽዕኖ ሲያሳደር ቆይቷል።
የመደመር መንግሥት ግን ይህን ቀይሮታል። ሀገር የመምራት ኃላፊነት ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ በከተማና በገጠር ሁለንተናዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ በዜጎች የኑሮ ሥርዓት ላይ ለውጥ ማምጣትን ግብ አድርጎ እየሰራ ነው
ከተሜነት ብቻውን አድጎ የገጠሩ ማኅበረሰብ በቀድሞ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሆነ የተሟላ ዕድገት ማምጣት አይቻልም የሚል ጽኑ እምነት አለው። በእዚህም ከተማና ገጠርን ለማቀራረብ በገጠር ትራንስፎርሜሽንን የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን ቀርጾ መተግበር ከጀመረ ከራርሟል።
የገጠር ትራንስፎርሜሽን አንዱ አካል የሆነው የገጠር ሞዴል መንደር በአርሶ አደሮች ዘንድ የሚጨበጥ ተስፋን ይዘው ከመጡ ኢኒሼቲቮች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ነው።
ከተስፋ ተሻግረው በዚህ ሞዴል መንደር የነዋሪነት ዕድልን ያገኙት ደግሞ ብርሃን አይተዋል፤ የትናት አኗኗራቸውን የቀየረ አዲስ ዛሬን በእጃቸው አድርገዋል፤ ነገን አልቀው መመልከት የግብርና ተግባራቸው አንዱ አካል ሆኗል።
በአዲሱ መንደራቸው ዛሬ የሚያፈስ ቤት የለም፣ የእንስሳት ቆሻሻ ሽታ በአፍንጫቸው አይገባም፣ በሚቆረቁር እንጨት ወይም መደብ ላይ አይቀመጡም፤ የከተሜው መዘነጫ ሶፋ በሳሎናቸው ተከስቷል። ጓሮዎቻቸው ሁሉ ሙሉ እንደሆኑ አፍ አውጥተው የሚያወሩ ናቸው።
በዚህ ቆስጣ፤ በዛ በኩል ጎመንና ቀይስር፤ ዘውር ሲሉ ደግሞ ከአስር የሚልቁ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች፤ በአንድ ክፍል ደግሞ እናት ላም ከጥጃዋ ጋራ፣ የእንቁላል ዶሮ ከሥጋ ዶሮ ጋር ሁሉንም በአንድ ጊቢ ውስጥ ያገኛሉ።
ምን ይሄ ብቻ አቮካዶ እና ፓፓያ፣ ሙዝና እንሰት፣ በርበሬና ሽንኩርት ሳይቀር ለተትረፈረፈ የአርሶ አደር ማዕድና ገበያ ራሳቸውን አዘጋጅተዋል።
አርሶ አደር ኃይሉ ሞትንሞስ በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ የጌሊት ሞዴል መንደር ነዋሪ ናቸው። እርሳቸው "መንግስት ጨለማችንን ገፎ ብርሃን አሳየን" ሲሉ በጠንካራ ቃላት የገጠር ሞዴል መንደር ፕሮጀክት ያመጣላቸውን በጎ ነገር ይገልጻሉ። እውነት ነው ያላዩትን ብዙ ነገር አሳይቷቸዋል።
ያም ብርሃን ቤት ውስጥ የሚበራ ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው፣ በነገ ተስፋቸውና በኢኮኖሚያቸው ላይ የፈነጠቀ ብርሃን ነው። ዛሬ ያሉበትን ህይወትም "ለእኔ አዲስ ነገር ነው። አይቼው አላውቅም፤ መቼም በራሴ ሀሳብ አላደርገውም ነበር።" ሲሉ ይገልጻሉ። መንግስት አበራልኝ ያልኩት በእጄ ያለኝን ያላየሁትን ዕድል ስላሳየኝ ነው በማለትም ሀሳባቸውን ይቀጥላሉ።
እኛ ሀብት አለን፤ ሀብታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ግን ትክክል አይደለም። ይልቁንም የምናባክነው ይበዛል በማለትም የቀደመ ሕይወታቸውን እያሰቡ ይቆጫሉ። አሁን ግን ብዙ ተገነዘብኩ የሚያስብል የመደመር መንግስት በመኖሩ አዲስ ሕይወት በአዲስ ተስፋ መጀመራቸውን ይገልጻሉ።
እርግጥ ነው የገጠር ሞዴል መንደር ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው። ለአብነትም የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማት ዝርጋታን ማንሳት ይቻላል። የተሠሩ ሞዴል መንደሮች በመጀመሪያ የመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ የመሆን ዕድል ገጥሟቸዋል።
በመቀጠል ንጽሕናው ያልተረጋገጠ የመጠጥ ውኃ ወንዝ ወርዶ ከመቅዳት ተቆጥበው በመንደራቸው የተገነባውን የከረሰ ምንድር ውሃ ከቧንቧ ቀድተው መጠጣት አስችሏቸዋል። በእሳት እና ኩራዝ ጭስ ሲሰቃዩ የነበሩ ዓይኖቻቸው ዛሬ ከሶላር ቴክኖሎጂ የመነጨ ብርሃን ማየት ጀምረዋል።
ብርሃን ብቻ አይደለም ለወትሮ ለገበያ ወደ ከተማ ብቻ ሲወጡ ይመለከቱ የነበረውን ቴሌቪዥን ዛሬ በቤታቸው አስገብተው የመረጃና የመዝናኛ ዓለምን ተቀላቅለዋል።
አርሶ አደሮቹ ቴሌቭዥንን ከመዝናኛነት ይበልጥ ለመረጃ እንደሚጠቀሙት ያነሳሉ። ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን በዜና ተከታትሎ መረዳት፣ የገበያ ሁኔታን ማወቅ፣ የግብርና ሥራ ተሞክሮን መቅሰምና የአየር ንብረት ሁኔታን ጨምሮ ለሕይወታቸው ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን የሚያገኙት ከቴሎቪዥን መስኮት እንደሆነ ይናገራሉ።
በጓሯቸው የተትረፈረፈ የሌማት ትሩፋት ምርት መሰብሰብ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ ደግሞ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ የጎላ ጠቀሜታ አለው። በተለይ መንግስት በጓሯቸው ጥምር እርሻ እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ የነገ ኢኮኖሚያቸውን በአስተማማኝ መሠረት ላይ የሚያስቀምጥ ነው።
ከተማን መናፈቅን ያስቀረው የገጠር ሞዴል መንደር ያኔ ከጅምሩ አመኔታን አላገኘም። የቦታና የአካባቢ ቁሳቁስ ለማቅረብ ዝግጁ እስካለመሆን የደረሱ አርሶ አደሮችም ነበሩ። በወቅቱ ጉዳዩን እንደፌዝ አዩት። ዛሬ ግን ውጤቱን በአግራሞት በዐይናቸው ተመለከቱ።
የተናገረውን የሚከውን፤ የጀመረውን የሚጨርስ የመደመር መንግሥትን ተጨባጭ ስራዎች በማረጋገጥ እንደ ትንግርት ቆጠሩ። ዛሬ በየአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች በቁጭት ተሞልተው መንደራቸውን ወደዚህ የሞዴል መንደር እሳቤ ለመቀየር ተነሳስተዋል።
የጌሊት ቀበሌ አርሶ አደሮቹ መኮንን አርዶ እና ነጻነት ተስፋሁን ለዚህ ተጠቃሾች ናቸው። ያዩትን ተሞክሮ በራስ አቅም በመንደራቸው ለማስፋፋት ማቀዳቸውን ተናግረዋል። ከተማ ሄደን የምናወጣውን ወጪና የምናባክነውን ጊዜና ጉልበት በማስቀረት እዚሁ መዝናናት የምንችልበትን ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ብለዋል።
"ይህ ዕድል ለእኛ ለአርሶ አደሮች በታሪክ የሚነገር ትልቅ አጋጣሚ ነውም" ይላሉ። በጤዛ እየራስን እንጓዝበት የነበረው መንገዳችን ዛሬ ሰፍቷል። ተሽከርካሪ በደጃችን ስለሚያልፍም ምቹ ዕድልን ይዞልን መጥቷል። ይህን ጅምር ተግባር ወደ ላቀ ውጤት ማሸጋገር የእኛ ድርሻ ነውና ጠንክረን እንሠራለንም ብለዋል።
ይህን ዕድል ወደ ትልቅ አቅም ለመቀየር መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ የሸሸቃ ሞዴል መንደር ተጠቃሚ አርሶ አደር አልዓዛር ዘርክናንስ ናቸው። የዶሮና የከበት እርባታን እንዲሁም ዘመናዊ የንብ ማነብ ሥራን ከመደበኛው የእርሻ ሥራ ጋር አስተሳስረው በመሥራት ከቤተሰብ ፍጆታ ተርፎ ለገበያ የሚበቃ ምርት ለማምረት እየተዘጋጁ ነው።
ይህም የገቢ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ ልጆቻቸው ወተትና የወተት ተዋጽኦ በቤታቸው እንዲያገኙ ያደርጋል። ማር፣ እንቁላል እና ሥጋ እንዳያምራቸው የሚያደርግ ትልቅ ኢኒሼቲቭም ነው። አንዱ ቢጎድል በሌላው እየሞሉ የሚኖሩበትን የሥራ መስክ አጠናክረው ለውጤት አብቅተው ለተሻለ ለውጥ እንደሚሠሩ አክለዋል።
የአርሶ አደር እናቶች ዘምቢል ይዘው አትክልትና ፍራፍሬ ሸመታ ወደ ገበያ ማቅናት የለባቸውም። ይልቁንም ከጎሮቸው ወደ ገበያ ይዞ መውጣት የኑሮ ዘዬያቸው ወግ ነው። ወይዘሮ መሠረት ማሞ በሸካ ዞን የኪ ወረዳ የበቆ ሞዴል መንደር ነዋሪ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ያልለመዱትን አዲስ ሕይወት ከአዲስ ተስፋ ጋር መጀመራቸውን ከሚናገሩት መካከል ናቸው።
ትናንት ኩሽናቸው፣ መኝታቸው እንዲሁም የከብትና የዶሮ ማደሪያ በአንድ ቤት ወስጥ የተወሰነ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬ ግን ሽንት ቤትና መታጠቢያ ቤት ሳይቀር ለየብቻ የራሱ የሆነ ቤት ተገንብቶ ጽዳቱ የተጠበቀ ኑሮ መኖር ጀምረዋል። ቤታቸው ሲገቡና ሲወጡ ለዓይን ማራኪ፤ ለመቀመጥ ምቹ፤ ለመተኛትም ንጹህና ወገብ የሚያሳርፍ ሆኖ አግኝተዋል።
እናም በዚህ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። "መንግስት እንደ አባት ጎዶሏችንን ሞልቷል" ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት ይህ የአርሶ አደሮችን ሕይወት ብሩህ ያደረገው የገጠር ሞዴል መንደር ኢኒሼቲቭ በመላው ሀገሪቱ በመስፋፋት ላይ ነው። ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 16 ሞዴል መንደሮች በ16 ወረዳዎች ተገንብተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለፁት ኢኒሺዬቲቩ የአርሶ አደር ኑሮ ዘዬን ከማሻሻል ባለፈ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ ጋር ለማቆራኘት ያስቻለ ነው። የተሻለ መኖሪያ ቤት ኖሮት በጓሮው የሚበላ ነገር ካጣ ሕይወቱ ትርጉም ያለው ለውጥ አያመጣም።
ይህም በመሆኑ ቤቶቹን ከእያንዳንዱ የግብርና ልማት ዘርፎች ጋር በማጣመር እንዲገነቡ የተደረገው። ይህም የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ በምግብ ራስን የመቻል ሀገራዊ ስትራቴጂን የሚያጠናክርና ገበያን የማረጋጋት ዓላማን የያዘ ጭምር ነው።
በገጠር ሞዴል መንደር ግንባታ የተገኘው መልካም ውጤት በቀጣይ በሁሉም ወረዳዎች የሚስፋፋ ሲሆን በዞን እና ወረዳ መዋቅሮች ድጋፍና ክትትል በቀበሌ ደረጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አንስተዋል።
ይህ ኢኒሼቲቭ የሀገራዊ ብልጽግና ጉዞ አንዱ አቅም ነው። የተደመረ የማኅበረሰብ ብልጽግና ሀገርን ከፍ ያለ የዕድገት ማማ ላይ ያስቀምጣታል። እነሆ የክልሉ አርሶ አደሮች የአካባቢያቸውን ጸጋ ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚ የሚቀይሩበት መስክ በሞዴል መንደር ምክንያት እጃቸው ላይ ደርሷል።
አርሶ አደሮቹ እንዳሉትም በብዙ መንገድ ጨለማ የከበበው የገጠሩ ማኅበረሰብ ሕይወት ዛሬ ብርሃን ማየት ጀምሯል። ይህ የብርሃን ፋና እየተቀጣጠለ ወደ ብዙኃኑ ሊደርስ የሁሉንም ፍላጎት አነሳስቷል። ሥሩ ከማለት ይልቅ ሠርቶ ማሳየትን የሚያስቀድመው የመደመር መንግስት የፈጠራቸው የገጠር ሞዴል መንደሮች ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን በዘላቂነት የሚያሳምሩ ናቸው።
ሰላም እንሰንብት!