የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የከተማዋ የብልፅግና ጉዞ ዋና ማዕከል ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የከተማዋ የብልፅግና ጉዞ ዋና ማዕከል ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ):- የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የከተማዋ የብልፅግና ጉዞ ዋና ማዕከል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
"ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል" በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን የአምስተኛ ዙር ሰልጣኞች አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማው ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር፤ የማዕከሉ ተመራቂዎች የመቻል ህያው ምስክር መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሰልጣኞቹ ቀደም ሲል መስራት እየፈለጉ ያልቻሉበትን፣ የመገፋትና የጥላቻ ህይወት ያስተናገዱበትን ጊዜ አሳልፈው ዛሬ ላይ ሕይወታቸው ታድሶ፣ በፍቅር ታንጸውና በተስፋ ተሞልተው የብርሃን ወጋገን ማየት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ሰልጣኞቹ በማዕከሉ በቆዩበት ጊዜ የስራ ባለቤት የሚሆኑበትንና ለሌሎችም የሚተርፉበትን አቅምና ክህሎት ማግኘታቸውን በመግለጽ፣ ነገ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ዕድልና ስኬት እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ውጤቱ እየጨመረ በመምጣቱ ከሀገር አልፎ ለሌሎችም ተምሳሌት እንሆናለን ብለዋል፡፡
ከተማዋንና ሀገርን ለማበልፀግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሰው ልጅ ዋና ማዕከል መሆኑንና የብልፅግናም ዋና ግብ የሕብረተሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሆነ አብራርተዋል።
የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሂርጳሳ ጫላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ የሚሹ ሴቶች የተሃድሶና የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በዚህም በአምስተኛው ዙር ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ 858 ሰልጣኞች ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል።
ሰልጣኞቹ የንድፈ-ሃሳብና የክህሎት ስልጠና አጠናቀው በወሰዱት የሙያ ብቃት ምዘና 95 በመቶ ያህሉ ማለፋቸውን አስረድተዋል።
ማዕከሉ ባለፉት አራት ዙሮች የሰለጠኑትን ጨምሮ እስካሁን በአጠቃላይ 3 ሺህ 259 ሴቶችን በተሃድሶና በሙያ ስልጠና ማብቃት መቻሉንም ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተቋሙ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እና መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 898 ተማሪዎች አስመርቋል ብለዋል።
የትምህርት እና የሥልጠና ጥራትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ አዳዲስ መደበኛ እና አጫጭር የሥልጠና ፕሮግራሞች ተቀርጸው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የጋራ ፕሮግራሞችን የማስተሳሰር ሥራ መሠራቱንም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
የልምድ፣ የክህሎት፣ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን እንዲሁም ከታዳጊነት ዕድሜ ጀምሮ የሙያ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበርም በፋሽን ኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ከመደበኛ ተመራቂዎች መካከል አስናቀች ወንድሙ እንደተናገረችው፤ ከመንግስት ስራ ባሻገር የራሷን ስራ ፈጥራ ሀገሯንና ወገኗን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ሌላኛዋ የማዕረግ ተመራቂ ብዙዬ ዝናቡ በበኩሏ፤ በትምህርት ቆይታቸው ከንድፈ-ሀሳብ ባሻገር ሰፊ የተግባር ትምህርት ማግኘታቸውን በመጥቀስ፣ በሙያዋ ሀገሯን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች።
ከደቡብ ሱዳን መጥታ ትምህርቷን የተከታተለችው ሰልጣኝ ረቢካ ኤንግል የኢትዮጵያ መንግስት የትምህርት እድል ስለሰጣት ምስጋናዋን አቅርባለች።
አክላም በቆይታዋ ከመደበኛው ትምህርት ባሻገር የኢትዮጵያን ብዙ ባህሎችና ወጎች ማወቅና መገንዘብ እንደቻለች ተናግራለች።