ቀጥታ፡

ብልፅግና ፓርቲ የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያከናውናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እንደሚያከናውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ በሚመሰርተው መንግስት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል።

በሀገር ደረጃ ትልቅ ምክክር እየተካሄደ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዘመናት ተከማችተው የቆዩ ችግሮች በአካታች ሀገራዊ ምክክሩ መፍትሔ በማግኘት ለሕዝቡ እፎይታ ይሰጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በኢኮኖሚው በኩል የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ በክልሎችም ሆነ በሀገር ደረጃ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተነሱት ሃሳቦች መካከል የአገልግሎት አሰጣጥን ማፋጠን፣ ሌብነትን ለማጥፋት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ተመራጮች ቃላቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ሕዝቡ አደራ መስጠቱንም ገልጸዋል። 

በተለይ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት በርካታ ሥራዎች እንደሚሠሩና የአገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማገዝ የሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ እንደሚሄዱ ነው ያብራሩት።

በቀጣይ በርካታ ትላልቅ ሥራዎች እንደሚሰሩ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአብነትም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኒውክሌር ኢነርጂ ለማመንጨት እየሰራች ሲሆን ይህም ውጤታማ ይሆናል ብለዋል። 

ይህ በአፍሪካ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ታስቦ የሚቀር ሳይሆን የሚፈጸም ሃሳብ በመሆኑ ለመጪው ትውልድ ትልቅ መሠረት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

ሕዝባችንን ከመሬትና ከግብርና ተግባሩ መነጠል አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለግብርና ደግሞ ትልቅ ግብዓት የአፈር ማዳበሪያ ነው ብለዋል። 

በዚህም ለአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ማሽኖች እየገቡ መሆኑን ጠቁመው የመስኖ ፕሮጀክቶችም በበርካታ ቦታዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ አንስተዋል። 

የመሬት ስፋትን በመጨመርና በክላስተር በማረስ የምርት መጠን ማደጉን ገልጸው ይህንን የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመስኖ በጋውን ሙሉና ክረምትም በበቂ ሁኔታ ማምረት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፤ ይህን ለማድረግ የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩንና ይህም ሙሉ ምላሽ ይሰጣል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ባለፉት ሀምሳና ስልሳ ዓመታት ተፈጥሮ ጋዝ ለማውጣት ትልቅ ጥረት ብታደርግም ተፈጻሚ ሳይሆን መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ በማውጣት የሁለትና የሦስት ፋብሪካ ግብዓት እየሆነ ይገኛል ብለዋል። 

በተወሰነ መልኩም የተፈጥሮ ጋዝ እያመረትን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካታ ናፍጣ ይጠቀሙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ተፈጥሮ ጋዝ እየተቀየሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። 

ከሁለትና ሶስት ወራት በኋላ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም እንጀምራለን የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ከሁሉም በላይ በቢሾፍቱ እየተገነባ የሚገኘው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል። 

የከተሞች መዘመንና የኮሪደር ልማት ሥራዎች የመጨረሻውና ዋናው ግባቸው ከተማዎችን ዘመናዊ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን፣ የተሻለ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን፣ ንጹህ ውሃን፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን እንዲሁም በቂ መብራቶችን ማግኘት የሚያካትት ነው ብለዋል። 

በተጨማሪም ማህበረሰቡ በአቅራቢያው የትምህርትና የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለትና አዳዲስ ፈጠራዎችን ማሳደግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው ከተሞችን የማዘመን ተሞክሮ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከአዲስ አበባ ውጪ በክልሎችም የተሻሉ ከተሞች ይኖሩናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም