ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የስብዕና ግንባታ ሰልጣኞችን አስመረቁ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለያየ ማህበራዊ ችግር ውስጥ የነበሩ በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በ5ኛ ዙር የክህሎት እና የስብዕና ግንባታ የሰለጠኑ 858 ሰልጣኞችን አስመረቁ።


 

ከንቲባ አዳነች፥በከተማችን ከምንሰራቸው ሰው ተኮር ስራዎች አንዱ ትላንት በጎዳና፣ በችግር እና በተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ የነበሩ ሴቶችን በሙያ ክህሎትና ስብዕና ገንብተን ከነበሩበት አስከፊ ህይወት በማውጣት ወደ ተሻለ ህይወት የምናሰማራበት ቀዳሚው ተግባር ነው ብለዋል።


 

አዲስ አበባችን ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት እንዲሁም ለዘመናት የከረሙ ስብራቶቿ የሚጠገኑባት ከተማ የማድረግ የተግባር ውጤት ፍሬ ማሳያዎች ከለነገዋ ተመርቀው አዲስ ህይወት እየመሩ ያሉት ሴቶች እህቶቻችን ናቸው ሲሉ ጠቁመዋል።

የዛሬዎቹ ተመራቂዎችን ጨምሮ በማዕከሉ በድምሩ 3259 ሰልጣኞችን አስመርቀን ወደ ስራው ዓለም እንዲቀላቀሉ በማድረግ ህይወታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲመሩና ለሌሎችም አርዓያ እንዲሆኑ አድርገናል።


 

አክለውም፥ውድ ተመራቂዎች አስከፊውን ትላንታችሁን አልፋችሁ፤በማዕከሉ በነበራችሁ ቆይታ በቀሰማችሁት ክህሎት እና ባገኛችሁት የተሀድሶ ስልጠና ዛሬ ማሸነፍ ችላችኋል ነው ያሉት።

ነገም በስራው ዓለም ስኬታማ ለመሆን የሚገጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና በማሸነፍ ህይወታችሁን ይበልጥ ብሩህ እንደሚያደርጉ ከንቲባዋ እምነታቸውን በመግለጽ የእንኳን ደስ አላቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም