የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ በተለያየ ምክንያት የደም እጥረት የሚያጋጥማቸውን ወገኖች ችግር ለመፍታት እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ በተለያየ ምክንያት የደም እጥረት የሚያጋጥማቸውን ወገኖች ችግር ለመፍታት እያገዘ ነው
ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ):-የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ በተለያየ ምክንያት የደም እጥረት የሚያጋጥማቸውን ወገኖች ችግር ለመፍታት እያገዘ መሆኑን በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የደም ባንክ አገልግሎት ገለፀ።
በድሬዳዋ አስተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወኑ ካሉ 14 የልማት ዘርፎች መካከል የደም ልገሳ፣ የበሽታ መከላከል ትምህርት እና ነፃ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሾች ናቸው።
በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ የደም ባንክ አገልግሎት አስተባባሪ ፋሲል ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጋና በክረምት ባህል እየሆነ በመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰበሰበው ደም ዕጥረትን በማቃለል መሰረታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በተያዘው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የህብረተሰቡን የደም ልገሳ ባህል በማጠናከር አስካሁን ድረስ ከ745 ከረጢት ደም በላይ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
ይሄ በጎ ተግባር በወሊድ ወቅት እና በድንገተኛ አደጋ ደም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ችግር በመፍታት ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የራሱን እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃድ ደም የለገሱ የመንግስት ሠራተኞችና ወጣቶች በበኩላቸው፤ የሚለግሱት ደም በደም ዕጥረት አንድም ሰው እንዳይሞት ስለሚያደርግ በተግባሩ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ አረጋሽ ንጉስ የለገሱት ደም ወላድ እናትን የሚታደግና ሕይወትን የሚያለመልም በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጤናማ ሰው በየሦስት ወራት ደም መለገስ እንደሚችል ባገኘሁት ግንዛቤ መሠረት በፍቃደኝነት ደም ለግሺያለሁ ያለው ደግሞ ወጣት አፈንዲ መሐመድ ነው።
በተለያዩ አደጋዎች ተጎድተው በሕክምና ተቋማት ተኝተው ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደራሽ መሆን መንፈሳዊ እርካታ የሚሰጥ መልካም ተግባር መሆኑን ተናግሯል።