ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን በምርት ዘመኑ ከ231 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ ቀረበ

አዶላ፤ ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ231 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ጣእምና ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለማእከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጉጂ ዞን በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቡና አምራች አካባቢዎች መካከል በጥራትና በምርት መጠን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ አካባቢ ነው፡፡ 

በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ዋጋ ከሚሸጡ የታጠቡና ያልታጠቡ የቡና አይነቶች መካከል የጉጂ ቡና ይጠቀሳል፡፡

በዞኑ የሚገኙ አነስተኛ አባወራ አምራቾች፣ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትና ባለሀብቶች በቡና መልቀም፣ ማጠብና ማድረቅ ሂደት ላይ ባላቸው ልምድ ምክንያት የምርቱን ጥራት ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዞኑ የተደረጉ የጥራት ቁጥጥር ስራዎች፣ የኮንትሮባንድ ንግድን የመግታት እርምጃዎችና አምራቾችን በቀጥታ ከማዕከላዊ ገበያ  ጋር የማገናኘት አሰራር ምርቱ በጥራትና በስፋት ለገበያ እንዲቀርብ አግዟል፡፡


 

በዞኑ ንግድ ጽህፈት ቤት  የእቅድና በጀት ባለሙያ አቶ ደረሰ ደንቆ በ2018 በጀት አመት ከዞኑ በጥራትና በብዛት የሚወዳደር የቡና ምርት ለማቅረብ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል፡፡ 

በእስካሁኑ ክንውንም ከዞኑ ቡና አምራች ወረዳዎች የተሰበሰበ 231 ሺህ 190 ኩንታል የተፈጥሮ ጣእምና ጥራት ያለው ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል ብለዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 174 ሺህ 100 ደረቅ እና 57 ሺህ 90 ኩንታል ታጥቦ የተቀሸረ የደረቅ ቡና ምርት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የተቋቋሙ በርካታ የደረቅና የእሼት ቡና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ቡናን በብዛትና በጥራት እያዘጋጁ በማቅረብ ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡ 

የጉጂ ቡና በጣእምና ጥራቱ ተመራጭና ተፈላጊ እየሆነ በመምጣቱ ከተለያዩ ቡና ላኪ ኩባንያዎች እውቅናና የምስክር ወረቀት መሰጠቱንም አስታውሰዋል፡፡

እውቅናው የዞኑ የተፈጥሮ ቡና ጣእምና ጥራቱን ሳይለቅ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መነሳሳት መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡

የዞኑ የቡና ልማት የሚከናወነው በተፈጥሮ ደኖች ጥላ ስር በመሆኑ ባለልዩ የተፈጥሮ ጣእም ባለቤት እንዲሆን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ አዶላ ከተማ የተቋቋመው የቡና ጣእምና ቅምሻ ማእከል ለምርት ጥራትና አቅርቦት መሻሻል መነሳሳት ፈጥሯል ብለዋል፡፡


 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ደስታ ገብረየሱስ በበኩላቸው መንግስት ለቡና ልማት የሰጠው ትኩረት  ምርታማነትን በተሻለ እያሳደገ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ 13 ወረዳዎች በቡና ልማት ከተሸፈነው ከ187 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት አብዛኛው በተሻሻለ የቡና ተክል የለማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ከሰብል ልማትና ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን ከ110 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት መሳተፋቸውንም አስታውቀዋል፡፡


 

በዞኑ አዶላ ወረዳ አንፈራራ ቀበሌ በቡና ልማት የተሳተፉት አቶ ገመዳ ሀለኬ ለልማቱ ትኩረት መሰጠቱ ምርታችንን በማሳደግ ተጠቃሚ አድርጎናል ብለዋል፡፡

ነባሩን የቡና ልማት በተሻሻለ ዝርያ በመተካት ብዛትና ጥራት ያለው ምርት በመሰብሰብ ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የተሻሻለው የቡና ዝርያ ምርታማነትን ከማሳደግ ሌላ ብርድና በሽታ በመቋቋም የተሻለ መርት የሚሰጥ መሆኑም እንዲሁ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም