ቀጥታ፡

ምክክሩ ለኢትዮጵያ ችግሮች ኢትዮጵያዊ መፍትሔ የሚያበጅ ነው- ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ችግሮች ኢትዮጵያዊ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት የሚያስችል ታሪካዊ መድረክ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ የሕዝብ ወኪሎችም በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

ይህ ሰፊ ተሳትፎን ያረጋገጠ መድረክ የዜጎችን ድምፅ በማሰባሰብ የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም፣ አብሮነት እና የጋራ መግባባት ምሰሶዎች ለማጽናት ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ወሳኝ መድረክ ነው።

ተመካካሪዎች በግልጽነት መንፈስ የሚያደርጓቸው ጥልቅ ውይይቶች ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት እንደሚጥሉ ይታመናል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች እንዳሉት፤ ምክክሩ የጋራ መግባባትን በማጠናከር እና ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

ከተመካካሪዎች መካከል አባ ገዳ ተሾመ በቀለ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግርና በዜጎች መካከል ያለውን ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ይህም ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ተሰባስበን የምናካሂደው እንደመሆኑ መጠን ልዩ ልዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱት በመከባበር እና በመደማመጥ መንፈስ ነው ብለዋል።

ይህ በታሪካችን ተደርጎ የማይታወቅ እና የዘገየ ቢሆንም በእኛ ዘመን ለሀገራችን ዘላቂ መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

ሌላኛዋ ተመካካሪ ነፃነት ሲሳይ በበኩላቸው፣ እጅግ አሳታፊ በሆነው በዚህ የምክክር መድረክ ሁሉም ተመካካሪዎች በንቃት በመሳተፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የሐሳብ ልዩነቶች ተፈጥሮአዊ መሆናቸውን በማንሳት አለመግባባቶችን በምክክር መፍታት ለቀጣይ ትውልድ የምትሆን ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ዘላቂ ሰላምን እና አብሮነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።


 

ተመካካሪ ዱናሞ ኡሞጎ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በሀገር ሰላምና ልማት ጉዳዮች ላይ በመምከር የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

በምክክሩ ላይ ለኢትዮጵያ ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ትክክለኛ ሐሳቦችን ማንጸባረቅ የተቻለበት ነው ብለዋል።


 

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም ያሳተፈ በመሆኑ ለሀገሪቱ ተጨባጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚያፈልቅ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ ተመካካሪ ተሰማ ላንዴቦ ናቸው።

የሀሳብ እና የመናገር ነጻነት በስፋት የሚንጸባረቅበት መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም