በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ እና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ እና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ እና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ-ግብር ያሠለጠናቸውን 1 ሺህ 898 ተማሪዎች አስመርቋል።
ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በምረቃ መርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የሪፎርም መስኮች ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ከእነዚህ መካከልም በጥናት፣ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በክህሎት ፓርኮች ግንባታ የተመዘገቡ ውጤቶች ዘርፉን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገራቸውን ገልጸዋል።
ዘርፉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና የገበያ ፍላጎትን የሚመልስ የሰው ኃይል በማዘጋጀት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ እውን የማድረግ ትልቅ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ብቃት ያላቸውን ሰልጣኞች ማፍራት የሚያስችሉ ተጨማሪ የክህሎት ፓርኮች እና መሠረተ ልማቶች እየለሙ እንደሚገኙም ሚኒስትሯ ጨምረው ጠቅሰዋል።
ተመራቂዎች ከሥራ ፈላጊነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት እንዲሸጋገሩ በመግለጽ፤ በፅናት፣ በዲሲፕሊን፣ በትጋትና በሀገር ወዳድነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተቋሙ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እና መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 898 ተማሪዎች አስመርቋል ብለዋል።
የትምህርት እና የሥልጠና ጥራትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ አዳዲስ መደበኛ እና አጫጭር የሥልጠና ፕሮግራሞች ተቀርጸው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የጋራ ፕሮግራሞችን የማስተሳሰር ሥራ መሠራቱንም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
የልምድ፣ የክህሎት፣ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን እንዲሁም ከታዳጊነት ዕድሜ ጀምሮ የሙያ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበርም በፋሽን ኢንዱስትሪና በሌሎች ዘርፎች ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።