ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ትውልድና ሀገር ለመገንባት መሰረት እየጣለ ነው-ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 3/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ትውልድና ሀገር ለመገንባት መሰረት እየጣለ ነው ሲሉ ተመካካሪ አባቶች ገለጹ።      

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።  

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

ከተመካካሪዎቹ መካከል አቶ ደረጀ ቦጋለ በሰጡት አስተያየት፤ምክክሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተና ከአራቱም ማእዘናት የተውጣጡ ብሄር ብሄረሰቦችን ያቀፈ መሆኑን አመልክተው፤ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እየገለጹ ነው ብለዋል።          

ምክክሩ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፤ ለትውልድ እና ለሀገር የሚበጅ እና ኢትዮጵያን የሚያሻግር መሠረት ለመጣል እየተመካከርን ነው ሲሉም ተናግረዋል።     

በምክክሩ የችግሮቻችንን ምንጭ በመለየት መፍትሄ የምናስቀምጥበትና እና ታሪክ የምንሰራበት ነው ብለዋል።  

ኢትዮጵያውያን ለእኔ ሚለውን ትተን ወደ እኛ ከመጣን ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትበቃለች ፤አንድነታችንን ካጠናከርን ኢትዮጰያን ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገር እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።    


     

ሌላው የምክክሩ ተሳታፊ አቶ ገበየው ደቦየ በበኩላቸው፤ምክክሩ ሀገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ለእድገትና ሰላም አስፈላጊ ነው ብለዋል።     

ምክክሩ የሀገር አንድነትን ለማጠናከር የጎላ አስተዋጽኦ አለው ያሉት አቶ ገበየው፤ ይህም ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።      

በጉባኤው የሚሳተፉ ተመካካሪዎች አደረጃጀት በስፋት ለመሳተፍ የሚያስችልና አካታች መሆኑን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አቶ አበራ ሞናሞ ናቸው።


  

የሀገር አንድነት ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ጠቁመው፤ ምክክሩ ለሀገር እድገትና ዘላቂ ሰላም ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።     

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም